የህወሓት ኃይሎች በደሴ ከተማ የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረጉ መሆናቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Dessie city communication/fb
በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወደሆነችው ደሴ መግባታቸው የተነገረው የህወሓት ኃይሎች ቤት ለቤት እየሄዱ ፍተሻ እያደረጉ መሆናቸውን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ገለጹ።
በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ ሲካሄድባት የነበረችው ደሴ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ውጥረት ነግሶባት የቆየች ሲሆን ቅዳሜ አማጺያኑ ከተማዋን ተቆጣጥረናል ቢሉም መንግሥት ግን አስተባብሎ ነበር።
አስካሁን ድረስ ደሴን በተመለከተ መንግሥት በግለጽ ያለው ነገረው ባይኖርም፣ አማጺያኑ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በእጃቸው መግባቷን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ዛሬ ያነጋገራቸው ነዋሪም የህወሓት ኃይሎች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎችን ለመያዝ ፍተሻ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪው በአሁኑ ጊዜ የደሴ ከተማ ፀጥ ያለች ሲሆን ከከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኙ ስፍራዎች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ እንደሚወራ፣ ነገር ግን የተኩስ ድምፅ አለመስማታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
በከተማዋ ያሉ የንግድ ቤቶች የተዘጉ ሲሆን የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገለግሎቶች መቋረጣቸውን ነዋሪው ጠቅሰዋል። ካለፈው አርብ ከሰዓት በኋላ አንስቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ቅዳሜ ዕለት ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም ገልጸው ነበር።
በተጨማሪም በደሴ ከተማ ያለ የስልክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን አንዳንድ ነዋሪዎች በከተማዋ ወዳሉ ከፍታ ቦታዎች በመሄድ ስልክ መደወል እንደቻሉ ሌሎች ነዋሪዎችም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የህወሓት ኃይሎች ደሴ ውስጥ እያካሄዱት ባለው የቤት ለቤት ፍተሻ ወቅት ነዋሪዎችን በቤታቸው ውስጥ የመንግሥት ወታደሮች የቤተሰብ አባላት መኖር አለመኖራቸውን እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
የፌደራሉ ሠራዊትና የህወሓት ኃይሎች በደሴ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ለሳምንታት የቆየ ከባድ ውጊያ ሲያደርጉ እንደቆዩ ሲዘገብ ነበር።
ከአዲስ አበባ 385 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የደሴ ከተማ በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ናት።
በትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክሎች ከተስፋፋ በኋላ ከሰሜን ወሎ በጦርነቱ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከተማዋ ተጠልለው ይገኙ ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት መልሶ ያገረሸው ውጊያ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተካሄደ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ቀናት ተቆጥረዋል።
ደሴ እና የኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ በአማጺያኑ እጅ መግባታቸው በተነገረበት ጊዜ የአማራ ክልል ምክር ቤት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅሙ የቻለ በሙሉ ያለውን መሳሪያ በመያዝ ወደ ግንባር እንዲዘምት ጥሪ አቅርበዋል።
የሰሜን እና የደቡብ ወሎ ዞኖቹ በርካታ አካባቢዎቹ በአማጺያኑ የተያዙበት የአማራ ክልል በተለይ "ማንኛውም የመንግሥት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ በጀቱን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የገጠመንን የህልውና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲረባረብ" ሲል ወስኗል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የህወሓት ኃይሎች ደሴንና ኮምቦልቻን መቆጣጠራቸውን በሚመለከት የሚወጡ ሪፖርቶች እንዳሳሰባቸውና ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ሊያራዝመው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ብሊንከን ጨምረውም ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ያለንም ቅድመ ሁኔታ ለተኩስ አቁም እንዲደራደሩ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የአማጺያኑ ኃይል አመራር የሆኑት ጄነራል ጻድቃን ድርድር እንደማይኖር እና በጀመሩት ዘመቻ እንደሚቀጥሉ መናገራቸው ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዛሬ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጸው የህወሓት ኃይሎች ከ100 በላይ ወጣቶችን ኮምቦልቻ ውስጥ እንደገደሉ አመልክቷል።
ይህንን በተመለከተ ከገለልተኛ ወገንም ሆነ ከአማጺያኑ በኩል የተሰማ ነገር የለም።
በመጪው ረቡዕ አንድ ዓመት የሚሞላው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ ወራት ተቆጥረዋል።















