በሆስፒታል የሚገኘው አርቲስት አሊ ቢራ "እየተሻለኝ ነው" አለ

ታዋቂው ድምጻዊ አሊ ቢራ ህመም አጋጥሞት ህክምና ላይ ይገኛል።
የ73 ዓመቱ አርቲስት አሊ ቢራ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች የህክምና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።
"በፊት ላይ በጣም አሞኝ ነበር። አሁን ተሽሎኛል። አሁን ያለሁበት ሆስፒታል ጥሩ ክትትል እያደረጉልኝ ስለሆነ ፈጣሪ ይመስገን እየተሻለኝ ነው" ብሏል አሊ ቢራ።
አሊ ቢራ በአሁኑ ወቅት የውስጥ ደዌ ህክምና እየተደረገለት ሲሆን ከዚህ ቀደምም የልብ እና የስኳር በሽታዎች ታማሚ መሆኑን ይናገራል።
"አንዳንድ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለ እኔ ሐሰተኛ ወሬ በማሰራጨት ሰዎችን እያስደነገጡ መሆኑን ሰምቻለሁ" የሚለው አርቲስት አሊ ቢራ፤ ሰዎች የመረጃዎችን እውነትነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብሏል።
ከአሊ ጎን የነበረችው የአሊ ባለቤት ሊሊን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያሰራጩት ሐሰተኛ ወሬ እጅጉን እንዳበሳጫት ለቢቢሲ ተናግራለች። ሰዎች ከዚህ መሰል ተግባራቸው እንዲቆጠቡም ጠይቃለች።
አሊ ቢራን ሆስፒታል ድረስ በመሄድ ያነጋገረው የቢቢሲ ሪፖርተር "አሊ ምንም እንኳ ታሞ የሆስፒታል አልጋ ላይ ቢገኝም መልካም ስሜት እና ጤነኝነት ፊቱ ላይ ይነበባል" ብሏል።
አሊ ቢራ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ስሜቱን እጅጉን ጎድቶት እንዸነበረ አልሸሸገም። "የዛ ልጅ ሞት እጅግ በጣም ጎድቶኛል . . . " ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ እምባ ቀድሞታል።
የአዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ኮሌጅ የጤና ባለሙያዎች ጥሩ እንክብካቤ እና የሕክምና ድጋፍ እያደረጉለት እንደሆነ አሊ ቢራ ይናገራል።
አሊ ቢራ ባለፉት 50 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ ቆይቷል። ለቋንቋ የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።














