የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቦርድ አባልነት ውዝግብ አስነሳ

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮችን፣ የኮሚሽነርና የቦርድ አባላት ሹመትን አጽድቋል።

በዕለቱ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ምክር ቤቱ ሹመት በመስጠትና በመንፈግ ላይ መጠመዱን በማንሳት ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባልነት የቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።

ለኢትዮጵያ የፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ከቀረቡ ዘጠኝ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ቅሬታ ያቀረቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዳሉት ከሆነ ግለሰቡ የሀይማኖት እኩልነት ላይ የማያምኑ፣ በዜጎች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር የሚሰሩ፣ በማለት በሕዝብ የሚነሱባቸው ቅሬታ ወደ ጎን በመተው መቅረብ አልነበረባቸውም በሚል አባልነታቸውን ተቃውመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መላውን ኢትዮጵያ የሚያገለግል በመሆኑ በእርሳቸው የቦርድ አባልነት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ከቀረቡት አባላት መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ቅሬታ በመቅረቡ ለብቻው ጉዳያቸው ታይቶ ድምጽ እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ በ148 ድጋፍ በ126 ተቃውሞ እና 24 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ የዲያቆን ዳንኤል የቦርድ አባልነት ፀድቋል።

ከዚህ በኋላ በቀሩት አባላት ላይ ድምጽ የተሰጠ ሲሆን በአብላጫ ድጋፍ ድምጽ በመመረጣቸው በሕዝብ ተወካዮቹ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል የነበሩትና አሁንም በአባልነት እንዲቀጥሉ የቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል በአብላጫ ድምጽ ከተመረጡ በኋላ በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሀላ ከፈፀሙ የቦርድ አባላት መካከል አልተገኙም ነበር።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የቀረበለትን የተለያዩ የሚኒስትሮች ሹመትንም ተቀብሎ አጽድቋል።

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ ላቀው አየለ፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ፊልሰን አብዱላሂ

የፎቶው ባለመብት, Fana Broadcasting corporate

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር፣ አቶ ላቀ አያሌው የገቢዎች ሚኒስትር፣ ወይዘሮ ፊልሰን አብዶላሂ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር በማድረግ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

በዛሬው እለት የተሾሙት ሚኒስትሮችም ሆኑ የፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባላት በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሹመት አጽድቋል። አቶ ፀጋ አራጌ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ተሾመዋል።

በምክር ቤቱ ውሎ ከቀረቡት ሌሎች ቅሬታዎች መካከል የብልጽግና ፓርቲ ሕጋዊነት ጉዳይ ከአንዳንድ አባላት የተነሳ ሲሆን ሌሎች የሕዝብ እንደራሴዎች ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሕግን በመጥቀስ የፓርቲውን ሕጋዊነት ተከራክረዋል።