የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን መልቀቅ ሲታወስ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, "የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ በፍቃዴ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ" ኃይለማርያም ደሳለኝ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር።

የካቲት 8/2010 ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለመልቀቅ ነበር ጥያቄ ያቀረቡት።

በወቅቱ ከድርጅት መሪነትና ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት "የሀገሪቱ ችግር የመፍትሄ አካል ለመሆን" ስለፈለጉ መሆኑንም ገልፀው ነበር።

ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን በመናገር ለኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀው ነበር።

"የኢህአዴግ ምክር ቤት ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተካኝን የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ይመርጣል ብየ አምናለሁ። በተመሳሳይ መንገድ ድርጅቱና መንግሥት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ በአገራችን ዳግም ታሪክ የሚሰራበት ወቅት ነው ብዬ አምናለሁ" ነበር ያሉት።

በወቅቱ ያስገቧቸው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዎች ውሳኔ እስከሚያገኙ በኃላፊነታቸው እንደሚቆዩም ተናግረዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም በመግለጫቸው ለሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች መፍትሄ ፍለጋ ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈው ነበር።

"ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቅረፍ መላው የአገራችን ህዝቦች ከዚህ በፊት የተለመደው ኢትዮጵያዊ የመቻቻል እና የመከባበር ሁኔታ እንዲቀጥል መስራት አለብን።"

ጨምረውም "በአገራችን ደኅህንት ዋስትና እኔም በበኩሌ የድርሻዬን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ" ብለው ነበር።

ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ከወረዱ በኋላም የዚምባብዌ ምርጫን እንዲታዘብ የተላከውን የአፍሪካ ሕብረት ልዑካን ቡድን በመምራት ወደ ወደዚያው በማቅናት ከቀድሞውን ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ተገናኝተው ፎቶ በመነሳታቸው የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ ቆይተው በሞት የተለዩት አቶ መለስ ዜናዊን በመተካት ሥልጣን የተረከቡት በመስከረም ወር 2005 ዓ. ም. ነበር።

የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆነንም ለስድስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

እርሳቸውንም በመተካት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፓርቲውንም ሆነ የአገሪቱን ሥልጣን መረከባቸው ይታወሳል።

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ያለቸው ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የነበረው ፍጥጫ ሲያበቃ ወደ አሥመራ ካመራው የኢትዮጵያ ቡድን ጋር ወደ ኤርትራ ተጉዘው ነበር።

አቶ ኃይለማሪያም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከአገር ውጪ ባሉ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አባል እንዲሆኑም ተመርጠዋል።

በዚህም መሰረት ከሚጠቀሱት ተቋማት መካከል በአፍሪካ የአረንጓዴ ልማት ጥረት ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርገውና በአስራ አንድ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚገኙ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማሻሻል በሚሰራው 'አሊያንስ ፎረ ኤ ግሪን ሪቮሉሽን ኢን አፍሪካ' የተባለው ድርጅት የቦርድ አባል ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱና ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን የሚከታተለው መንግሥታዊ ያልሆነው 'ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ'ም የቡድኑ የቦርድ አባል እንዲሆኑ በቅርቡ መርጧቸዋል።