የቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተናዎች

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

የገዥው ፓርቲ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከመጋቢት ሁለት እስከ መጋቢት አስር ድረስ ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባውን ጀምሯል።

ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ በሰጠው መግለጫ በሃገሪቱ ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን "የአመራር ድክመት የወለዳቸው" ሲል የገለፃቸው ሲሆን ይህንን ለማረም የሚያስችል "አመለካከት እና አንድነት" የሚፈጥር ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጡንም ተናግሯል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው ከአንድ ወር በፊት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተክቶ ፓርቲውን በሊቀ መንበርነት፤ ኢትዮጵያን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያስተዳድሩትን መሪ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው እውን የአዲስ መጭው ጠቅላይ ሚኒስትር የቤት ስራዎች ምን ምን ናቸው? የሚለው ነው።

"እኔ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የምጠብቀው የፍትህ ስርዓቱን እንዲያሻሻል ነው። በተለይ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን ችለው ያለምንም ጫና ውሳኔ መስጠት የሚለችሉበትን አቅም መፍጠር እንዳለበት አምናለሁ። ሲሉ የኢህአዴግ ምርክ ቤት ስብሰባ መቋጨትን በጉጉት እየጠበቁ እንዳሉ የነገሩን የድሬዳዋ ነዋሪ ያስረዳሉ።

አክለውም "የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚሰማቸውን በመናገር እንዲሁም የሕዝቡን ድምፅ በማስተጋባት ከቀድሞው የተለየ አካሄድ ሊከተሉ ይገባል። ካልሆነ ግን ለኔ 'ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥ' እንዳይሆን እሰጋለሁ" ይላሉ።

ፖለቲካው ላይ ወደሚሳተፉ አቅንተን ያናገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት ሕዝቡ በፍላጎቱ በመረጠው ፓርቲ ሲተዳደር መሆኑን ይናገራሉ።

ፓርቲያቸው በህዝብ ምርጫ አብልጦ እንደሚያምን የሚገልፁት አቶ የሽዋስ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የተለየ ፖለቲካዊ አቋም ካላቸው ወገኖች ጋር ለውይይት መቀመጥን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራና ተቋማዊ ማሻሻዎችን ለማድረግ የሚተጋ መሪ ቢመረጥ ለሃገሪቱ የሚበጅ ነው ይላሉ።

ከተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነት በበለጠ ይዟቸው የሚመጣቸው ኃሳቦች እንደሚያሳስቧቸው የሚናገሩት አቶ የሽዋስ ተስፋቸው የተቆጠበ መሆኑ ግን አይደብቁም።

"ኢህአዴግ ከዚህ በፊት በሚጠቀምባቸው ዘዴዎችም ሆነ ማስፈራሪያዎች ሊገዛ አይችልም። ማንም ቢሆን የሚመጣው ማንነቱ ሳይሆን የሚያጓጓን ይዞ የሚመጣው ነገር ምንድነው? ምን ያህልስ የህዝቡንድ ድምፅ ለመስማት ዝግጁ ነው። ይህ ነው እንጂ ኢህአዴግ አንድ ድርጅት አንድ ሥርዓት ስለሆነ የተለየ ነገር በጣም በጉጉት የምንጠብቀው ነገር የለንም።"

"አዲስ ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ተደቅነው የሚጠብቁት ውስብስብ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ብሎም ለመቅረፍ የፖለቲካ ዝግጁነት፣ ቁርጠኝነት እና አቅም እንዳለው ማሳየት ይገባዋል" የሚሉት ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እና የደህንነት ጉዳዮችን የሚያጠኑት ተመራማሪው ለአቶ ሃሌሉያ ሉሌ ናቸው።

"በዋነኛነት ህዝቡ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ጥያቄ እንግዲህ የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ይመስለኛል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማሕበረሰብ ቷቋማት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት እንዲሁም ሃሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት መድረክ ማግኘትን የሚደግፉ የህገ-መንግስቱ አንቀፆች የሚከበሩበት ምህዳር እንዲፈጠር ማድረግ ትልቁ የቤት ሥራ ነው ብዬ አስባለሁ።"

አቶ ሃሌሉያ አክለውም "የጦር ሰራዊቱና የደህንነትና ስለላ ተቋማት ለህገ-መንግሥቱ እንዲሁም ለፓርላማ አባላት ያላቸው ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንዲሁም የሃገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ-መንግሥት እንደሚያዘው በእነዚህ ተቋማት ወስጥ ያለውን የብሄር ተዋፅኦ ማረጋገጥ አስፈላጊም አስቸኳይም የቤት ሥራ ይመስለኛል" ይላሉ።

አቶ ሃሌሉያ ሉሌ ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝቡ ዘንድ ለተነሱ ጥያቄዎች ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር፤ ምላሽ የሚቀርብበት ግልፅ የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት፤ ይህም የሕዝቡን ትዕግስት ለማግኘት እንደሚጠቅመው ጨምረው ተናግረዋል።

ምሁሩ ሃሳባቸውን ሲያጠናቅቁ ካለፉት ጥቂት ዓመታት አንስቶ በአገሪቱ ለሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስ ገፊ ምክንያቶች እና ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል እንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ሊመለሱ የሚችሉ ቢሆኑም ሌሎቹ ደግሞ ዘለግ ያለ ጊዜን የሚሹ መዋቅራዊ መፍትሄዎችን ይፈልጋሉ ይላሉ።

ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝቦች ላነሷቸው ጥያቄዎች ዕውቅና ከመስጠትም ባሻገር ምላሽ የሚቀርብበት ግልፅ የጊዜ ሰሌዳ ማስቅመጥ እንደሚጠበቅበት ይህም የሕዝቡን ትዕግስት ለማግኘት እንደሚጠቅመውም ይከራከራሉ።