የድኅረ ዐብይ ሚዲያ ምን ያህል ነፃ ነው?

ቢሰጥ አያሌው (ዶ/ር) የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ ዳዊት አሞኝ (ዶ/ር) የሂውማኒቲስ ፋካሊቲ ኃላፊ እና አደም ጫኔ (ዶ/ር) የሂውማኒቲስ ፋካሊቲ

የቢቢሲ አማርኛ ባልደረቦች በተለያዩ ስፍራዎች ጉዞ በማድረግ ከተለያዩ የማህብረሰብ ክፍል አባላት ጋር በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች በማድረግ ላይ ናቸው።

ከነዚህም አንዱ ትናንት ሰኞ የካቲት 25 ረፋድ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ተዘጋጅቶ ነበር።

የውይይቱ ዋነኛ ጭብጥ የነበረውም ወደ ስልጣን ከመጣ አንድ ዓመት ለመድፈን የተቃረበው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተዳደር ስኬቶች እና ተግዳሮቶች ምንድናቸው? የወደፊት አቅጣጫውስ? የሚል ሲሆን ትኩረቱንም በመገናኛ ብዙሃን ላይ አድርጎ ነበር።

በውይይቱ ላይ ቢሰጥ አያሌው (ዶ/ር) የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ ዳዊት አሞኝ (ዶ/ር) የሂውማኒቲስ ፋካሊቲ ኃላፊ እና አደም ጫኔ (ዶ/ር) የሂውማኒቲስ ፋካሊቲ ምክትል ኃላፊ በመወያያ ርዕሱ ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩ ሲሆን፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና መምህራን የውይይቱ ታዳሚዎች ነበሩ።

ውይይቱ የተጀመረው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የታዩት በጎ ለውጦች ምንድናቸው በሚለው የመወያያ ጥያቄ ነበር።

ዶ/ር አደም በመገናኛ ብዙሃን ዙሪያ ታይተዋል ካሏቸው ለውጦች መካከል የሚዲያ ምህዳሩ መከፈት መጀመሩን በዋናነት ያነሳሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ወደ 20 የሚጠጉ አዲስ የህትመት እና የብሮድካስት ሚዲያዎች መፈጠራቸውን እና ከሃገር ውጪ የነበሩ መገናኛ ብዙሃን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን የሚዲያው ምህዳር እየሰፋ ስለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን ዶ/ር አደም ይናገራሉ።

''ከዚህ በተጨማሪ አይነኬ ይባሉ የነበሩ ጉዳዮች በመንግሥት ሚዲያዎች ሁሉ ሲቀርቡ እያየን ነው፤ በርካታ ድምጾችም እየተሰሙ ነው። ይህም የሚዲያው ምህዳር እየሰፋ ስለመሆኑ ያሳያል''ይላሉ።

ዶ/ር ዳዊት በበኩላቸው ባለፉት 12 ወራት በመገናኛ ብዙሃን ከታዩት ለውጦች በተጨማሪ በማህበራዊ ሚደያዎች አጠቃቀም ላይ ለውጥ መምጣቱን ይናገራሉ። ዶ/ር ዳዊት ሃሳባቸውን ሲያስረዱ ሰዉ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተሰማዉን ስሜት በነጻነት እያጋራ ይገኛል ይላሉ።

በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ የሆነው ሙሉቀን አሰግደው ይገኝበታል። ሙሉቀን ባለፉት 12 ወራት ውስጥ የታዩትን ለውጦች ከዚህ ቀደምም መንግሥታት ሲለወጡ እንመለከተ የነበረው አይነት ለውጥ ነው ይላል።

ከታዳሚዎቹ መካከል

''ከዚህ ቀደም ከነበረን ታሪክ እንደምረዳው መንግሥታት ሲቀየሩ፤ አዲስ መንግሥት ሲመጣ ሚዲያውን የመክፈት ባህሪ አላቸው። ሚዲያዎች አዲስ የመጣውን መንግሥት ማጀገን፤ ያለፈውን ደግሞ ማሳጣት ሥራዬ ብለው ይያያዙታል። መንግሥትም ሚዲያዎቹ ፊታቸውን ወደእሱ እስኪያዞሩ ድረስ በይሁንታ ይዘልቃል'' ሲል ሃሳቡን ያስቀምጣል።

ሙሉቀን ጨምሮም የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደርም ለሚዲያዎች ምን ያክል ክፍት መሆኑ የሚፈተነው ከአሁን በኋላ በሚኖሩ ሁነቶች ነው ይላል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደስልጣን ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በመገናኛ ብዙሃን ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው? የሚለው ጥያቄ የውይይቱ ተሳታፊዎች የተነጋገሩበት ርዕሰ ጉዳይ ነበር።

ዶ/ር አደም ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ተፈጥሯል ያሉትን የሚዲያ ምህዳሩ መስፋት ሊመጥን የሚችል የባለሙያ እጥረት አለ ይላሉ። ''በስነምግባሩ የታነጸ፣ ሙያውን የሚያከብር ብዙ ጋዜጠኛ አለን ወይ?''ሲሉ ይጠይቃሉ።

አክለውም ''የሚዲያ ፍልስፍና ስለመኖሩ ከመንግሥት በግልጽ አልተነገረንም'' የሚሉት ዶ/ር አደም፤ ''ከዚህ ቀደም የነበረው ኢህአዴግ ባህሪው ሚዲያ ጠል ነበረ። ይህም ከሚከተለው 'ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ርዕዮተ አለም' ጋር አብሮ ይሄዳል። አሁን ለውጡ ስርዓታዊ መሆን ይኖርበታል።'' በማለት ይናገራሉ።

ከሚዲያው በተጨማሪ ማህበረሰቡም የሚቀርቡለትን መረጃዎች በአስተዋይነት እና በጠያቂነት ባህሪ ሊያጤናቸው እንደሚገባ ዶ/ር አደም ምክር ይለግሳሉ።

ዶ/ር አደም በሃገራችን መገናኛ ብዙሃን ዙሪያ ሌላው እንደ ችግር ብለው የሚያነሱት ጉዳይ ክልላዊ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ጽንፍ የያዙ ዘገባዎችን በስፋት እያስተናገዱ መምጣታቸውን ነው። ''ከዚህ ቀደም በኢሳት እና ኢቲቪ መካከል እንመለከት የነበረውን ዓይነት በክልል ሚዲያዎች እየታዘብን ነው'' ይላሉ።

ፅንፈኝነት ማቆጥቆጥ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ሚዲያ ተግዳሮት፤ የምርመራ ጋዜጠኝነት ትኩረት ማጣት እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየፈጠሩት ያሉት ጫና ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

''አክቲቪስቶች ለሚዲያዎች ርዕሰ ጉዳይ ሲሰጡ እያስተዋልን ነው'' የሚሉት ዶ/ር ዳዊት መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ሚዲያ እና በአክቲቪስቶች ተጽዕኖ ሥር የመውደቅ ምልክትን እንደ ትልቅ የሙያ ጉድለት ያነሱታል።

ከጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል የመጣው ስንታየሁ በበኩሉ ''በሃገራችን ያሉት መገናኛ ብዙሃን ሳይሆኑ የህዝብ ግንኙነት ተቋሞች ናቸው'' ይላል። ለዚህም እንደ ማጣቀሻ የሚያነሳው የክልል ሚዲያዎች የሚወክሉት እና የሚያንጸባርቁት የክልል መንግሥቱን ፍላጎት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎችም ተመሳሳይ መንገድ እንደሚከተሉ ያስረዳል።

"ሚዲያው ብዙኃኑን ከመከተልና የተመረጡ ጉዳዮችን ብቻ ከመሸፈን ድምጻቸው ላልተሰማ ትኩረቱን መስጠት ይኖርበታል።"ይላል።

መዋቅራዊ የሆነ አሰራር ባለመኖሩና የግለሰቦችን አጀንዳ ሲያራግቡም እንደሚታዩ ስንታየሁ ይናገራል። ከዚህም ውስጥ እንደ ምሳሌ የሚያነሳው በአንድ ወቅት አንድ አቀንቃኝ (አክቲቪስት) ያለውን ጉዳይ ነው።

''አክቲቪስቱ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ላይ ከመቅረቡ የተነሳ ጋዜጠኞችን ለምንድነው ሥራ የማትሠሩት ለምንድነው ስለ እኔ ብቻ የምታወሩት ሲል እስከመገስጽ ተደርሷል''

ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ታዳሚዎች መካከል

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደስልጣን ከመምጣታቸው በፊት መገናኛ ብዙሃን በሁለት ጽንፍ ተለጥጠው የቆዩ ነበሩ የሚሉት ደግሞ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ዘላለም ተስፋየ ናቸው።

''በመንግሥት እና በግል ሚዲያዎች ዘገባ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነበር። ዘገባዎቹ ጽንፍ የያዙ ነበሩ። መካከል ላይ እውነታውን የሚያሳይ አልነበረም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደስልጣን ከመጡም በኋላ ይህ ባህሪ እንዳለ ነው። የተቀየረ ነገር የለም።'' ይላሉ።

ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም ከላይ የተጠቀሱት ስኬቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ተስፋ ሊያስቆርጥ እንደማይገባ ዶ/ር አደም ይናገራሉ። ሚዲያውን አስረው የቆዩ ህጎችን መቀየር፣ ጠንካራ የሚዲያ ተቋማትን መገንባትና በራሳቸው እንዲቆሙ ማድረግ፣ ለጋዜጠኝነት ሙያ ትኩረት መስጠት እና ለጋዜጠኞች እና ለሚዲያ ተቋማት ተገቢውን የህግ ከለላ ማድረግ፣ የሚዲያ ካውንስል ማቋቋም ይደር የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ተወያዮቹ በዝርዝር አስቀምጠዋል።