የቢቢሲ አማርኛ የመጀመሪያ ዝግጅት በኢትዮጵያ ምድር

ከየካቲት 25 እስከ መጋቢት 07/2011 ዓ.ም ድረስ የቢቢሲ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ አዘጋጆች በየአካባቢው ያሉ ታዳሚዎችበሚኖሩባቸው ከተሞች በመገኘት በቀጥታ ለማግኘትና ለመወያየት ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች አቅንተዋል።
ለቢቢሲ በአይነቱ የመጀመሪያው በሆነው በዚህ ልዩ ዝግጅት ህብረተሰቡ የሚሳተፍባቸው ውይይትና ክርክሮች እንዲሁም አዳዲስ መሰናዶዎች በየዕለቱ ለታዳሚው የሚቀርብ ይሆናል።
በ2010 ዓ.ም የተጀመሩት እነዚህ የቢቢሲ አገልግሎቶች ለታዳሚዎቻቸው ቅርብ የሆኑ በርካታ ታሪካዊ ክስተቶች ሲዘግቡ ቆይተዋል።
ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ዝግጅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ አንድ ዓመት ሊሆናቸው በተቃረበበት ጊዜ በመሆኑ፤ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቃኘት አጋጣሚውን ፈጥሯል።
በተጨማሪም የመጀመሪያዋ ሴት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የነበሩትና አሁን የመጀመሪያዋ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ከሆኑት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የሃገሪቱ ተጠቃሽ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር የተደረጉ ቃለምልልሶች ይቀርባሉ።
ለ11 ቀናት በሚዘልቀው በዚህ ዝግጅት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙት ታዳሚዎች ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ተከታታይ መሰናዶዎች ይቀርባሉ። ወጥ ዝግጅቶቻችንን በሬዲዮ፣ በፌስቡክና በቢቢሲ አማርኛ ድረ ገፃችን ላይ ታገኟቸዋላችሁ።
የዚህ ዝግጅት ማጠቃለያ የሚሆነውም ሦስቱም ቋንቋዎች በጋራ ቅዳሜ መጋቢት 07/2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሃሰተኛ ዜና (ፌክ ኒውስ) ላይ በሚያዘጋጁት ውይይት ይሆናል።
የቢቢሲ የምሥራቅ አፍሪካ ሃላፊ ሬቼል አኪዲ እንደምትለው "የጋዜጠኝነት ሥራችንን በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነችውና በርካታ ወጣቶች በሚገኙባት ኢትዮጵያ ውስጥ ማስተዋወቅ እንፈልጋለን። በዚህ ዝግጅትም በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለመቃኘትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመዳሰስ እንችላለን። ይህም ታዳሚዎቻችን ስለኢትዮጵያ የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።"
//Ends
ሃሽታግ: #ቢቢሲአማርኛወደእናንተ መጥቷል/#ቢቢሲኒውስአማርኛ/ #ሙሉታሪኩንያግኙ
የፌስቡክ ገጻችን:
BBC News Amharic
ተጨማሪ መረጃ: ለቃለመጠይቅና ማወቅ የሚፈልጉት ነገር ካለ ከቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ግሩፕ ኮምዩኒኬሽ
ቢቢሲ ኒውስ አፍሪካ በተለያዩ ቋንቋዎች አህጉሪቱን የሚመለከቱ ዝግጅቶችን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በድረ ገጽ ያቀርባል። ቢቢሲ ካሉት የቋንቋ አገልግሎቶች መካከል አማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ይገኙበታል።













