ቢሊየነሩ ማይክል ብሉምበርግ በመጭው የአሜሪካ ምርጫ እወዳደራለሁ አሉ

የኒውዮርክ ከንቲባ የነበሩት ቢሊየነሩ ማይክል ብሉምበርግ እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በአሜሪካ በሚካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ በመሆን እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።
የ77 ዓመቱ ማይክል ብሉምበርግ "ዶናልድ ትራምፕን አሸንፌ አሜሪካን ዳግም ለመገንባት ነው የምወዳደረው። ይህን ምርጫ የግድ ማሸነፍ አለብን " ብለዋል።
ማክይል ብሉምበርግ በውሳኔያቸው ትራምፕን ለመፎካከር የተዘጋጁ 17 ዴሞክራት ተወዳዳሪዎችን ተቀላቅለዋል።
እስካሁን ባለው የኦባማ ቀኝ እጅ የነበሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፣ ሴናተር ኤሊዛቤት ዋረን እና በርኒ ሳንደርስ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የፊት መስመር አጥቂዎች ናቸው።
ቢሊየነሩ ብሉምበርግ ግን አሁንም የዴሞክራቶች ቡድን በሚገባ ትራምፕን የሚገዳደር አይደለም የሚል ስጋት አላቸው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዶናልድ ትራምፕ "ትንሹ ማይክልን እንደ መወዳደር የምፈልገው ነገር የለም" በማለት ቢሊየነሩ ማይክል ብሉምበርግን ነቁረዋቸው ነበር።













