ሩሲያ የአሜሪካንን ምርጫ ኢላማ ልታደርግ እንደምትችል የሲአይኤ ሃላፊ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty
የሲአይኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት አጋማሽ ላይ የሚደረገውን የአሜሪካ ምርጫ ሩሲያ ኢላማ ታደርጋለች የሚል ስጋት መኖሩን ገለፁ።
ሩሲያ በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ የምትሰነዝረው ጥቃት እየቀነሰ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
ሲአይኤ ባለፈው ዓመት በተደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች ብሎም ያምናል።
በተጨማሪም ዳይሬክተሩ ሰሜን ኮሪያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አሜሪካ ላይ የሚሳኤል ጥቃት የመሰንዘር አቅም ይኖራታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ማይክ ፖምፒዮ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት ብቁ ነኝ ብለው አያምኑም ነበር የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርገዋል።
"የዓለም ምርጡ የስለላ ድርጅት ነን። ለአሜሪካ ህዝብ ስንል ምስጢር እንሰርቃለን" ብለዋል ፖምፒዮ ለቢቢሲ።
በያዙት ሃላፊነት አንድ ዓመት ያስቆጠሩት ፖምፒዮ ሥራቸው የሲአይኤን አቅም ማሳየት እንዲሁም የድርጅቱን ሸክም ማቅለል እንደሆነም ገልፀዋል።
ምንም እንኳ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ትብብር ቢኖራቸውም፤ ፖምፒዮ ሩሲያን በቀዳሚነት የሚመለከቷት በአደገኝነቷ ነው። ሩሲያ አውሮፓና አሜሪካ ላይ የምታደርገው ጥቃትም ይህ ነው በሚባል መልኩ እየቀነሰ እንዳልሆነም አስረድተዋል።
በመጭው ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ ትገባለች የሚል ስጋት ቢኖራቸውም ግን ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ በማድረግ አገራቸው እርምጃውን እንደምትገታው እምነታቸውን ገልፀዋል።
በትራምፕ ብቃት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ስላስነሳው 'ፋየር ኤንድ ፊዩሪ' መፅሃፍ ተጠይቀውም መፅሃፉ ትራምፕን የሳለበት መንገድ የተሳሳተ ነው ብለዋል።
"ግራ የገባው ነው። መፅሃፉን አላነበብኩትም የማንበብ ሃሳቡም የለኝ" ብለዋል ፖምፒዮ።












