ሂላሪ ክሊንተን "በሚቀጥለው ምርጫ በጭራሽ አልወዳደርም ማለት አይቻልም"
![ሂላሪ ክሊንተን [ቀኝ] እንግሊዝ ውስጥ ከልጃቸው ቼልሲ ክሊንተን [ግራ] ጋር በጋራ የፃፉትን መፅሐፍ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/161AF/production/_109634509_hi057943545.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, PA Media
ሂላሪ ክሊንተን በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የአሜሪካ ምርጭ እንዲወዳደሩ የሚሹ ሰዎች ከፍተኛ ጫና እያሳደሩባቸው እንደሆነ አሳውቀዋል።
ሂላሪ ክሊንተን እንግሊዝ ናቸው። ከልጃቸው ቼልሲ ክሊንተን ጋር በጋራ የፃፉትን መፅሐፍ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
የባለፈው ምርጫ የዴሞክራቶች ዋነኛ ተወካይ እና የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ የነበሩት ሂላሪ እንደው በእርግጥ በሚቀጥለው ምርጫ ይሳተፋሉ ወይ? ተብለው በቢቢሲ ተጠይቀዋል።
የ72 ዓመቷ ሂላሪ እሳቸው ባለፈው ምርጫ ቢመረጡ ኖሮ ነገሮችን እንዴት ሊከውኑ ይችሉ እንደነበር ሁሌም እንደሚያስቡ አልሸሸጉም።
በግሪጎሪ አቆጣጠር 2020 ላይ ለሚካሄደው ምርጫ 17 ዕጩዎች ዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር እየተፋለሙ ይገኛሉ።
የቢቢሲ ራድዮ 5 ጋዜጠኛ የሆነችው ኤማ ባርኔት 'በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ይወዳደራሉ ወይ?' ስትል ለክሊንተን ጥያቄ አቅርባለች።
«ባለፈው ምርጫ ብምረጥ ኖሮ ለአገሬም ሆነ ለዓለም የተሻለ ነገር አደርግ እንደነበር ሁሌም አስባለሁ። አላስብበትም ማለት አይቻልም። ማንም አሸነፈ ማን በሚቀጥለው ዘመን ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል። ብዙ የተሸነቆሩ ቀዳዳዎችን መሸነፈን አለበት።»
እርግጡን ምላሽ እንዲነግሯት ወጥራ ለያዘቻቸው ኤማ፤ ሂላሪ ክሊንተን እንዲህ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋታል።
«አንድ ነገር ልንገርሽ፤ በጣም ብዙ ሰዎች በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ እንድሳተፍ ይወተውቱኛል። እኔም ሁሌም እላለሁ፤ በጭራሽ አልወዳደርም ማለት አልችልም። ግን አሁን ካንቺ ጋር ቁጭ ብዬ እያወራሁ ባለሁበት ቅፅበት ስለመወዳደር አላስብም።»
ሂላሪ ክሊንተን የውጭ ጉዳይ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። የኒው ዮርክ ግዛት እንደራሴም ነበሩ። ባለቤታቸው ቢል ክሊንተን አገሪቱን በፕሬዝደንትነት ሲመሩ ደግሞ ቀዳማዊ እመቤት።
ለሚቀጥለው ምርጫ የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ኤሊዛቤት ዋረንና ጆ ባይደን ቀዳሚዎቹ ናቸው። አዛውንቱ በርኒ ሳንደርስም የዋዛ ተቀናቃኝ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቀም።













