የሞኒካ ሊዊኒስኪና የክሊንተን የወሲብ ቅሌት ታሪክ በፊልም ሊሰራ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢል ክሊንተን ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ለሥራ ላይ ልምምድ ቢሯቸው መጥታ ከነበረችው ሞኒካ ሊውኒስኪ ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውን ተከትሎ ስለመጣው የ1999ቱ ከስልጣን ይውረዱ ሙግት በድራማ መልክ ተሰርቶ በአሜሪካ ቴሌቪዥን ለእይታ ሊበቃ ነው።
ይህ የወንጀል ታሪክ ለእይታ የሚበቃው የሚቀጥለው ዓመት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊደረግ በተቃረበበት ወቅት ነው ተብሏል።
የሊዊኒስኪ ድራማን ፕሮዲውስ የሚያደርጉት ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም የኦጄ ሲምፕሰንን የችሎት ሂደትና የጊያኒ ቬርሳኬ ግድያን በድራማ መልክ ለእይታ ያቀረቡ መሆናቸው ተገልጿል።
በድራማው ላይ ሊዊኒስኪን ወክላ የምትጫወተው ቤኒ ፈልድስቴይን ነች።
ሳራ ፖልሰን በወቅቱ በነጩ ቤተመንግሥት (ዋይት ሐውስ) ውስጥ ሰራተኛ የነበረች ሲሆን ሊዊኒስኪ ከቢል ክሊንተን ጋር የምታደርጋቸውን የግል የስልክ ጥሪዎች በሚስጥር በመቅዳት ያጋለጠች ናት፤ እርሷን በመወከል ደግሞ ሊንዳ ትሪፕን እንደምትጫወት ታውቋል።
እስካሁን ቢል እና ሂላሪ ክሊንተንን ወክለው የሚጫወቱ ተዋናዮች እነማን እንደሆኑ አልታወቀም።
ድራማው የተፃፈው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2000 በጄፍሪ ቶቢን ተጽፎ ለህትመት በበቃው መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ተነግሯል።
ሊዊንስኪ ስለድራማው መሰራት ተጠይቃ "እርግጠኛ" እንዳልሆነችና "ከፍርሀት ትንሽ የዘለለ ስሜት እንደሚሰማት" መናገሯ ተገልጿል።
ነገር ግን ከፕሮዲውሰሩ ጋር በስራው ላይ እራት እየበሉ ለረዥም ሰዓት መነጋገራቸው ገልፃለች።

የፎቶው ባለመብት, William J Clinton Presidential Library
አክላም " እስከዛሬ ድረስ ሰዎች የኔን ታሪክ መርጠው እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ ሲናገሩ ቆይተዋል" በማለት " እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ታሪኩን በራሴው አንደበት መናገር እንዳለብኝ ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር" ብላለች።
" በታሪክ አጋጣሚ ዝም እንድል ተደርጌ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ድምጼ እንዲሰማ ማድረግ በሚያስችል መልኩ እንደማህበረሰብ ስለተጓዝንበት መንገድ ደስተኛ ነኝ።"
ማክሰኞ ዕለት ድራማውን የሚያስተላልፈው ቴሌቪዥን፣ ኤፍኤክስ ሾው፣ ሰብሰሳቢ ጆን ላንድግራፍ ድራማው የአሜሪካ ምርጫ ሊደረግ ሲቃረብ መተላለፉ ላይ የሚነሱ ትችቶችን አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
" ይህ የወንጀል ታሪክ ቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም" ካሉ በኋላ ቢልም ሆነ ሂላሪ ክሊንተንን በድራማው ላይ ግብዓት እንዲኖራቸው እንደማያናግሯቸው ገልጠዋል።
ሊውኒስኪ አሁን 46 ዓመት የሆናት ሲሆን የ22 ዓመት ወጣት እያለች ነበር በ22 ዓመት ከሚበልጣት ቢል ክሊንተን ጋር የፍቅር ግንኙነት መስርታ የነበረው።
ባለፈው ዓመት ሊውኒስኪ የቢል ክሊንተንን ድርጊት "ከፍተኛ ሥልጣንን በአግባቡ ያለመጠቀም ድርጊት" ስትል የገለፀችው ሲሆን "የተሻለ ለማወቅ በቂ የሕይወት ልምድ ነበረው" ብላለች።
የቀድሞው ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ከሞኒካ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መጀመሪያ ላይ ክደው የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው የአሜሪካን ሕዝብና ባለቤታቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል።












