የአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማሕሬዝ የወሰደው መድሃኒት ጉዳይ አያሳበኝም ብሏል

ሪያድ ማሕሬዝ የወሰደው መድሃኒት ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አልጄሪያዊው እግር ኳሰኛ ሪያድ ማሕሬዝ በአፍሪቃ ዋንጫ ወቅት ወስዶታል በተባለ መድሃኒት ምክንያት የኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ ላይ ሳይሰለፍ ቀርቷል።

የአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማሕሬዝ መድሃኒቱን የወሰደው ከአፍሪቃ ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ በመሆኑ ብዙም አሳሳቢ አይደለም እያለ ነው።

ፌዴሬሽኑ 'ይህ የማንቸስተር ሲቲ ችግር ነው' ሲሉ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽኑ እንዳይላከክ አሳስበዋል።

የ28 ዓመቱ አልጄሪያዊ ማሕሬዝ ሃገሩን በአምበልነት እየመራ ግብፅ ላይ የተካሄደውን የአፍሪቃ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

ማሕሬዝ ባለፈው አርብ ነበር ወደ ክለቡ ማንቸስተር ሲቲ የተመለሰው። ቢሆንም እሁድ በተካሄድ የኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ ላይ መሳተፍ አልቻለም።

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ጉዋርዲዮላ 'ማሕሬዝ ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ መሳተፍ ያልቻለው የወሰደው መድኃኒት ምንነት ስለማይታወቅ ነው። ኃላፊነት መውሰድ ደግሞ አልፈለግንም' ሲሉ ተደምጠዋል።

አሰልጣኙ አክለው፤ 'ዶክተሮች መድኃኒቱን ማግኘት አልቻሉም' ሲሉ ከጨዋታው በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

እንደ ጉዋርዲዮላ አገላለፅ ማሕሬዝ ጨዋታው ላይ ቢሳተፍ ኖሮ ምናልባትም በአበረታች መድኃኒት [ዶፒንግ] ምክንያት ሌላ ጣጣ ውስጥ ይገባ ነበር።

ማሕሬዝ ሲቲ ከዌስትሃም ጋር ላለበት የመጀመሪያው የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።