ለሰው ልጆች በወጣ ሕግ ወደ አሜሪካ የተወሰደችው የዝንጀሮ ዝርያ

ለሰው ልጆች በተሰጠ መብት ወደ አሜሪካ የተወሰደችው የዝንጀሮ ዝርያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አርጀንቲና በሚገኝ የእንስሳት ማቆያ ውስጥ ለ20 ዓመት የኖረች የዝንጀሮ ዝርያ ወደ አሜሪካ እንድትወሰድ ተወስኗል።

'ኦራንጉቱን' የተባለችው የዝንጀሮ ዝርያ አሜሪካ በሚገኝ የእንስሳት ማቆያ እንድትገባ የተወሰነው የሰው ልጆችን ብቻ ለመጠበቅ የወጣ ሕግን መሰረት በማድረግ ነው።

ሳንድራ የሚል ስም የተሰጣት የዝንጀሮ ዝርያ፤ ቦነስ አይረስ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ተይዛ እንደቆየች በመግለጽ፤ ጠበቆች ሲከራከሩላት ነበር። ክርክሩን አሸንፈውም ዝንጀሮዋ አሜሪካ ገብታለች።

ውሳኔው፤ በአርጀንቲና ታሪክ ለሰው ልጆች የወጣ ሕግን ተመርኩዛ ነፃ የወጣች የመጀመሪያዋ ዝንጀሮ ያደርጋታል።

ኤሌና ሊበራቶሪ የተባሉት ዳኛ እንዳሉት፤ ውሳኔው የሰው ልጆች የእንስሳት መብት ማክበር እንደሚገባቸው ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የዝንጀሮ ዝርያዋ የተወለደችው በምሥራቅ ጀርመን በሚገኝ የእንስሳት ማቆያ ሲሆን፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1995 ለቦነስ አይረስ ተሽጣ ነበር። ለዓመታት ተገልላ እንድትኖር መደረጓም ተዘግቧል።

ሳንድራ የሚል ስም የተሰጣት የዝንጀሮ ዝርያ፤ ትኖርበት የነበረው የእንስሳት ማቆያ፤ እንስሳትን በማሰቃየት ክስ በ2016 ተዘግቶ ነበር። ለእንስሳት እንክብካቤ የሚደረግበት ማቆያ ይሆናል በሚል ዳግመኛ እንደሚከፈት ተገልጿል።

የዝንጀሮ ዝርያዋ አሜሪካ በምትኖርበት የእንስሳት ማቆያ ውስጥ፤ ከሷጋ ተመሳሳይ ዝርያ ካላቸው 21 እንስሳት ጋር የምትኖር ሲሆን፤ በነፃነት የምትንቀሳቀስበት ቦታ ተዘጋጅቷል።

ኦራንጉቱን የሚባሉት ዝንጀሮዎች በዓለም ላይ ዝርያቸው ከተመናመነ እንስሳት መካከል ይገኙበታል።