አፍሪካ የተሰጣትን ጨለምተኛ እይታ ለመቀየር ያለመው አዲስ ፎቶ ፌስት

በአፍሪካ ውስጥ ስመጥር ከሆኑት የፎቶ ፌስቲቫሎች ከፍተኛ ቦታ ያለው አዲስ ፎቶ ፌስት በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተከፍቷል።
ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ61 ሃገራት የተውጣጡ 152 የፎቶ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ይህ አውደ ርዕይ በየአመቱ አሳታፊነቱ እየጨመረ የመጣ እንደሆነ የምትናገረው የአዲስ ፎቶ ፌስት ዋና አዘጋጅና የፎቶ ባለሙያ አይዳ ሙሉነህ ዋና ትኩረቱም የውክልና ጉዳይ ነው ትላለች።
አፍሪካ በተለያዩ ምስሎችም ሆነ በውጭው ዓለማት የምትታወቀው ሁሌም ከችግር፣ ድርቅና ረሀብ ጋር ብቻ ከመሆኑ አንፃር ይህ ፎቶ ፌስትም በጎ ጎኗንም ለማሳየት እንዳለመ አይዳ ታስረዳለች።
"ይህንን የፎቶ አውደ ርዕይ የምናየው እንደ አቅም ግንባታ ነው። እነዚህን ሁሉ ወጣት የፎቶ ባለሙያዎች ስናሰባስብ ወይም ስልጠና ስንሰጥ የኢትዮጵያን ዕውነታ በምን መንገድ ሊያሳዩ ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት" እንደሆነ ትናገራለች።
በተለይም አፍሪካ እንደ ጨለምተኛ ብቻ አህጉር ተደርጋ መታየቷ ትክክለኛ እይታ እንዳልሆነ የምትናገረው አይዳ "ሁሉም ነገር በጎ አይደለም ነገር ግን ሁሉም ነገር ደግሞ መጥፎ አይደለም። በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጎልተው ገኖ የሚታየው መጥፎ ነገር ነው" ይህንንም ለመቀየር ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ ፎቶ ባለሙያዎችን ማፍራትና እይታዎችንም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ትሰጣለች።

በዚህ ዓመት ዓውደ ርዕይ 1200 ፎቶዎች የሚቀርቡ ሲሆን ከአመት ወደ አመት የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተናገራለች።
በባለፈው አመት ለመሳተፍ የጠየቁ የፎቶ ባለሙያዎች ቁጥር 500 የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ወደ 832 ደርሷል። ከነሱም ውስጥ 152 ባለሙያዎች ተመርጠው ተሳታፊ ሆነዋል። ለአይዳ ሙሉነህ የተሳታፊዎች ቁጥር መብዛት የሚያሳየው አዲስ ፎቶ ፌስት በአለም ላይ ያለው ስፍራ እየጨመረ መሆኑን ነው።

በተጀመረበት ወቅት አምስት የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ያሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 35 እንደደረሱ አይዳ ትናገራለች። ምንም እንኳን በፈተናዎች የተሞላ መሆኑን አይዳ ባትክድም "ይሄን ሁሉ ስራ የምንሰራው ሃገሪቷን ለማሳወቅ ነው" ትላለች።












