ቴሬሳ ሜይ በሶሪያ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ለመምከር ምክር ቤቱን ጠሩ

የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፣ በሶሪያ ደረሰ የተባለውን የኬሚካል ጥቃትን በተመለከተ የእንግሊዝ መንግስት ምላሽ ምን መሆን እንዳለበት ለመምከር ለምክር ቤቱ ጥሪ አቀረቡ።

ሚንስትሮቹ፣ አሜሪካና አጋር ሀገሮቿ እንወስዳለን ያሉትን ወታደራዊ እርምጃ መከተልን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ።

የቢቢሲ ምንጮች እንደተናገሩት፣ ጠቀላይ ሚኒስትሯ የፓርላማ አባላቱን ሳያማክሩ በሶሪያው ባሽር አልሳድ አገዛዝ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጠው ተነስተዋል።

አጋር ሀገራቱ በሶሪያዋ ከተማ ዱማ ዳግም ጥቃት እንዳይከሰት መከላከል ይሻሉ፡።

የሶሪያው ፕሬዚዳንት ባሽር አልሳድ ደረሰ የተባለውን የኬሚካል ጥቃት እውቅና ባይሰጡትም፣ ቴሬሳ እንደሚናገሩት "ጥቃቱ ስለመድረሱ መረጃዎች አሉ"።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው በሶሪያ ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ ዝተዋል።

የእንግሊዙ ምክር ቤትም ሀገሪቱ ሶሪያ ላይ እርምጃ እንድትወስድ ከወሰነ፤ የእንግሊዝ ወታደሮች ሶሪያን ኢላማ ያደረገውን ወታደራዊ እርምጃ ይቀላቀላሉ።

ትራምፕ፣ ሩስያ በአጋር ሀገሯ ሶሪያ ላይ ለሚደርሰው የሚሳኤል ጥቃት እንድትዘጋጅ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም፤ እሮብ እለት በተሰጠ መግለጫ የሗይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ የተለየ ሀሳብ አንፀባርቀዋል፡፡

ቃል አቀባይዋ በፕሬዚዳንቱ እጅ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ጠቅሰው "ከአማራጮቹ መሀከል ተግባራዊ የምናደርገውን ገና አላሳወቅንም " ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቴሬሳ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዊት ላይ አስተያየት ከመስጠት ታቅበዋል፡፡

ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮች መገንዘብ እንደተቻለው፣ ጠቅላይ ሚንስትሯ ከህዝብ ተወካዯቻቸው ጋር መክረው ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ፣ ትራምፕ ማንኛውንም እርምጃ እንዳይወስዱ ለመጠየቅ ወስነዋል።

የህዝብ ተወካዮቹ ከፋሲካ እረፍት በሗላ ወደ ስራ የሚመለሱት ሰⶉ ነው።

ቴሬሳ፣ በሙሉ ልብ ጣታቸውን በሶሪያው የአሳድ አገዛዝ ላይ ባይቀስሩም፤ የሃገሪቱ መንግስት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እርምጃ መውሰድ የግድ መሆኑን አመላክተዋል።

የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘጋቢው ጄምስ ላንደል እንደገለፀው ምክር ቤቱ የህዝብ ተወካዮችን ውሳኔ ይደግፋል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ጠቀላይ ሚንስትሯ ያለ ፓርላማው ድጋፍ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው፡፡

ሆኖም የጠቀላይ ሚንስትሯ ውሳኔ የሌበር ፓርቲ ሀላፊ ጀርሚ ኮርቢን ጨምሮ ብዙዎችን እንደሚያስቆጣ ጄምስ አክሏል፡፡በብዙሀኑ እምነት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የፓርላማው ውሳኔ መጠበቅ አለበት፡፡

ጀርሚ የቦምብ ጥቃት ማድረስ፣ በሶሪያ ያለውን ሁኔታ እንደሚያባብስም አሳስቧል፡፡

በአንፃሩ ቴሬሳ፣ የኬሚካል ጥቃቱ "በሰብአውያን ላይ የተቃጣ ከባድ አደጋ" መሆኑን በመግለፅ "እርምጃ ሳይወሰድ ሊታለፍ አይገባም" ብለዋል፡፡