በአማራ ክልል ሰሞኑን የተካሄደው የጅምላ እስር ምክንያት እና የፈጠረው ስጋት

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአማራ ክልል ባለሥልጣናት በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በሚል ባካሄዱት ዘመቻ ከ4500 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሳውቀዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የተጀመረው ይህ ዘመቻ ከአወዛጋቢው በግለሰቦች እጅ ያሉ የጦር መሳሪያዎችን ከመመዝገብ ጋር ነበር አብሮ የተካሄደው።
ይህንን ዘመቻ ለምን ማካሄድ እንዳስፈለገ ባልተደለመደ ሁኔታ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የክልሉ ፕሬዝዳንት ይልቃል ከፋለ፣ የክልሉ የገጠርና የከተማ አካባቢዎች ለሕዝቡ ደኅንነት ስጋት በደቀነ ሁኔታ "በሕገ ወጥ አንዳንድ ጊዜም በታጠቁ ግለሰቦች ምክንያት ሕገ ወጥ ድርጊቶች" እየተስፋፉ ናቸው ብለው ነበር።
ይህን ዘመቻ ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ምክንያት በተከሰተ ግጭት ችግር አጋጥሞ ነበር።
የማኅበረሰብ አንቂዎች በሞጣ፣ በመራዊ እና በወልዲያ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ግድያ ተፈጽሟል በማለት ይከሳሉ። የእስር እርምጃዎች አሁንም ድረስ መቀጠሉም እየተነገረ ነው።
እነማን ናቸው የታሰሩት?
በፀጥታ ኃይሎች ከተያዙት መካከል ተጠቃሽ የሆኑት ከወራት በፊት ከህወሓት ኃይሎች ጋር በአማራ ክልል ውስጥ በተደረገው ጦርነት የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ አንዱ ናቸው።
ጄነራሉ ልዩ ኃይሉን እንዲመሩ የተሾሙት የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው ጦርነቱ በተባባሰበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነበር።
በዚህ ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ የፌደራሉና የክልል ኃይሎች የህወሓትን ግስጋሴ በመግታት ወደ ትግራይ እንዲመለስ ለማድረግ ቻሉ። ብዙም ሳይቆይ ብ/ጄነራል ተፈራ ከክልሉ ባለሥልጣንት ጋር ባለመግባባታቸው ከልዩ ኃይሉ የመሪነት ቦታ እንዲነሱ ተደረገ።
ከዚያም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ በመንግሥት ላይ ትችት ይሰነዝሩ ነበር።
በተጨማሪም ቢያንስ አስር ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ ለአስር ተዳርገዋል። እስሩም አዲስ አበባና ባሕር ዳር ውስጥ የተካሄደ ሲሆን በዚህም መንግሥት በተቺ ድምጾች ላይ ሌላ ዙር ማሳደድ እያካሄደ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተካሄደውን ጅምላ አስር የተቸ ሲሆን፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ስንት ሰዎች እንደታሰሩ፣ የት እንዳሉ በግለጽ አለመታወቁና አንዳንዶችም በቤተሰብ አለመጎብኘታቸው ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዳሉት ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል 210 የሚሆኑት ግድያን በመሳሰሉ ወንጀሎች ተከሰው ሲፈለጉ የቆዩ ናቸው።
ከ40 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከእስር ቤት ያመለጡ መሆናቸውን ገልጸው በተጨማሪም "በመንግሥት እና በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ሆነው በወንጀል ተግባራት ሲሳተፉ የነበሩ" የተባሉ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
ነገር ግን በክልሉ ውስጥ ያሉ ተቺዎች ዘመቻው ሕገ ወጥንነትን ለመቆጣጠር እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ሳይሆን ፋኖ እየተባለ የሚታወቀውን ታጣቂ የወጣቶች ስብስብን ለመቆጣጠር የሚካሄድ ሰፊ ሙከራ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፋኖ ማን ነው?
በአሁኑ ወቅት የሚታየው የፋኖ የወጣቶች እንቅስቃሴ በአማራ ክልል ውስጥ እየጎለበተ የመጣው ከአምስት ዓመታት በፊት መካሄድ በጀመረው ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ ወቅት ነበር።
በዚያ ወቅት ፋኖ በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው ተመሳሳይ ፀረ መንግሥት የወጣቶች እንቅስቃሴ ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄደው ተቃውሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ለቀው ዐቢይ አሕመድ ወደ መሪነት እንዲመጡ አስተዋጽኦ ነበረው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በነበሩት ወራት በወቅቱ ያልታጠቀው የወጣቶች እንቅስቃሴ የነበረው ፋኖ፣ በኦሮሚያ ክልል ካለው አቻው የቄሮ እንቅስቃሴ ጋር በተለያዩ መድረኮች ላይ የለውጡ ወኪሎች ተደርገው ሲወደሱ ነበር።
ከለውጡ በኋላ በአገሪቱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ በተለይም አናሳ ቁጥር ያላቸው አማሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃቶች በበረቱበት ጊዜ፣ መንግሥት ጥቃቶችን ለመከላከል አልቻለም ወይም አልፈለገም የሚል ስሜት በወጣቶች ዘንድ ተፈጠረ።
በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የፋኖ ቡድኖች መደራጀት ጀመሩ።
ከሚታወቁት የፋኖ ቡድኖች መካከል የአንዱ መሪ የሆነው ዘመነ ካሴ በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገረው "አማሮች ለመከላከል" መደራጀትና መታጠቅ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጿል።
19 ወራትን ያስቆጠረው ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ ይህንን ሂደት አፋጥኖት ቡድኑ ከክልሉ እና ከፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ጋር በመጣመር ወደ ጦርነቱ ውስጥ ገባ።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል መስፋፋት ወጣቶቹን እራሳቸውን አደራጅተው በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ፋኖ የበለጠ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ እድል ፈጠረለት።
"ጠመንጃን ፀጥ የሚያሰኘው ብቸኛው ነገር ፍትህ ነው" ሲል ባለፈው ሚያዚያ ወር ለቢቢሲ የተናገረው ዘመነ፣ "አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ በሆነበት ዓለም፣ ሁልጊዜም ጠመንጃ አማራጭ ይሆናል" ብሏል።
የፋኖ ቡድኖች ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ሲከሰሱ ቆይተዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባለፈው ሚያዝያ ወር በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ ፋኖና ሌሎች የአማራ ክልል ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ በዘር ማጽዳት ድርጊት ከሰዋል።
አንዳንዶቹ የፋኖ ቡድን አባላት ሰዎችን መጥለፍን ጨምሮ በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ይከሰሳሉ።
አሁን ለምን?
ባለሥልጣናት የሕግ ማስከበር ያሉትን ዘመቻ እያካሄዱ ያሉት በአማራ ክልል ብቻ አይደለም።
ባለፈው ወር የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣንት መንግሥት ሽብርተኝነት በሰየመውና ሸኔ በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን ገልጸውነበር። ይህ ዘመቻም ድሮንን ያካተተ የአየር ጥቃት ጭምር የተፈጸመበት እንደነበር ይነገራል።
በመጋቢት ወር ላይ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል የታወጀውን የተኩስ ማቆም ተከትሎ፣ መንግሥት በሁለቱ የአገሪቱ ክልሎች በአማራና በኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ይመስላል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት ለማቆም የተደረሰ ስምምነት የለም።
በሁለቱ ወገኖች በኩል ሊደረግ የሚችል ስምምነት በአማራ ክልል ኃይሎች ስር በሚገኙትና ከትግራይ ጋር የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ምክንያት በአማራ በኩል በጥርጣሬ ሊታይ ይችላል። ይህም ተቃውሞን ሊያስከትል እንደሚችል ባለሥልጣናት መገመትና እርምጃ መውሰዳቸው አይቀርም።
ይህ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ግጭትን ከቀሰቀሰ ደግሞ፣ የተባበሩት መንግሥታት በተራዘመው ጦርነትና በከባድ ድርቅ ምክንያት በዚህ ዓመት 20 ሚሊዮን እርዳታ የሚያስፈልገው ሕዝብ ላለባት ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል።















