ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ የኦነግ አባላት በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈቱ ኢሰመኮ ጠየቀ

በእስር ላይ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Human Rights Commission

በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላት በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።

በተጨማሪም ሌሎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረው ያሉ አባላትም የሚያሳምን ክስ ካልቀረበባቸው ሊፈቱ እንደሚገባ ኢሰመኮ ዛሬው ግንቦት 11/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የጠየቀ ሲሆን፣ "የተራዘመ ቅድመ ክስ እስር ሰዎች በፍትሕ አስተዳደር ላይ ያላቸውን እምነት ያጠፋል" በማለት አፅንኦት ሰጥቷል።

በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የሚገኙት ስድስት የፓርቲው አባላት አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ ገዳ ገቢሳ ሲሆኑ ኮሚሽኑም ግለሰቦቹን ለማናገርም ችሏል።

ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣ አቶ አብዲ ረጋሳ ገላን በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ቤተሰብ እና ጠበቆቻቸው ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

ሌላኛው የኦነግ አባል አቶ በርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ህመም በፖሊስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ኮሚሽኑ ስሙን ባልጠቀሰው የህክምና ተቋም በህክምና ላይ የነበሩ መሆናቸውን አስፍሯል።

ኢሰመኮ በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች በእስር ላይ ያሉ የኦነግ አባላት የእስር ሁኔታን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ክትትል ማድረጉን እንዲሁም ከፓርቲው እና ከእስረኞች ከቀረቡለት አቤቱታዎች በመነሳትምበቡራዩ ከተማ፣ በገላን ከተማ እና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችንና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላትን በማናገር ይህንን የምርመራ ሪፖርት እንዳጠናቀረ አስታውቋል።

ኢሰመኮ እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤት እና በዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ውሳኔዎችን እና ትዕዛዞችን እንዲሁም የህክምና ሰነዶችንም መርምሯል።

የኮሚሽኑ የምርመራ ውጤትም እንደሚያስረዳው አባላቱ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነጻ የተሰናበቱ፣ ምንም አይነት ክስ ያልተመሰረተባቸው እና ዐቃቤ ሕግ ክስ የማይመሰርትባቸው መሆኑን በማረጋጋጥ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ናቸው ብሏል።

በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ የኦነግ አባላት ከወራት እስከ 2 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ሕግን ባልተከተለ መልኩ የታሰሩ፣ የተወሰኑትም በእስር ቆይታቸው ተገቢ ባልሆነ መልኩ የተያዙ፣ ድብደባ የተፈጸመባቸውና የአካል ጉዳቶችና ሌሎች የጤና እክል ያጋጠማቸው መሆኑንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመልክቷል።

እስረኞቹ በተያዙበት፣ በፖሊስ ምርመራ ወቅትና በእስር ቤት ቆይታቸው ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለኢሰመኮ አስረድተዋል።

ከነዚህም እስረኞች መካከል አንደኛውና ኢሰመኮ በስም ያልጠቀሳቸው እስረኛ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በአዋሸ መልካሳ ጊዜያዊ እስር ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ድብደባ ጭንቅላታቸው ላይ እንደተፈነከቱና እግራቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በእስር ቦታ መጨናነቅ፣ በንጽህና ጉድለት፣ በምግብ እጥረት፣ በህክምና እጦት ምከንያት ለህመም ተጋልጠናል እንዲሁም የአካል ጉዳትም ደርሶብናል ብለዋል።

ሪፖርቱ የኢሰመኮን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው ተገቢ ባልሆነ አያያዝ ምክንያት በእስረኞቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ካሳን ጨምሮ ሌሎች ሊደረጉ የሚገባቸውን ምክረ ሐሳቦችን ጠቁሟል።

"የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ የሚገባ ሲሆን፤ በተጨማሪም የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል" ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የግንባሩ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ ለረጅም ጊዜ በቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ያሉበት ሁኔታ እንዲስተካከል የፀጥታ አካላትን ጠይቆ ሊቀመንበሩ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር መደረጉ ይታወሳል።