በሶማሌ ክልል በባህላዊ የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያ ኢሰመኮ ኮነነ

ጂግጂጋ ከተማ
የምስሉ መግለጫ, ጂግጂጋ ከተማ

በሶማሌ ክልል ቦምባስ ከተማ በባህላዊ ሥነ ሥርዓት የጎሳ መሪ ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በፀጥታ ኃይሎችና በታጠቁ ግለሰቦች በተፈጸሙ ጥቃቶች የ11 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮነነ።

በሶማሌ ክልል ከሚገኙት የሶማሌ ጎሳዎች መካከል የሆኑት የአኪሾ ጎሳ አባላት መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የጎሳ መሪያቸውን ለመምረጥ በተሰበሰቡበት ዕለት ከግድያ በተጨማሪ 33 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ኢሰመኮ ዛሬ ግንቦት 04/2014 ዓ.ም. ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በስፍራው ተገኝቶ ባደረገውም ምርመራ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ አካላት ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ለሞትና ለአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ኢሰመኮ በሁለቱ ቀናት ስለተፈጸሙ ግድያዎችና የአካል ጉዳቶች የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ በቦታው በመገኘት የዓይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማናገሩን አስታውቋል።

በተጨማሪም ከሆስፒታል ምንጮች መረጃ በማሰባሰብ እንዲሁም ፈቃደኛ የሆኑ የክልሉ ኃላፊዎችን በማነጋገር የምርመራውን ሪፖርት አጠናቅሯል።

በተጨማሪም ቦምባስ ከተማ የሚገኝ የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን መካነ መቃብር መጎብኘቱን ገልጾ በዚህም በመጀመሪያው ቀን የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር እንዲሁም በሁለተኛው ቀን የተገደለች ሴት ተቀብራበታለች የተባለ መካነ መቃብር መመልከቱንም በዚሁ የምርመራ ሪፖርቱ አካቷል።

የግጭቱ መነሻ

ለዚህ ግጭት መነሻ የሆነው በፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ፣ ቦምባስ ከተማ የሚኖሩ የአኪሾ ጎሳ አባላት የራሳቸውን የጎሳ መሪ ከመምረጥ ጋር በተያያዘ እሰጣገባ ነው።

በሶማሌ ክልል የሚገኙ አብዛኛዎቹ ጎሳዎች የየራሳቸው የጎሳ መሪ እንደሚመርጡት ሁሉ የአኪሾ ጎሳ አባላትም የምርጫ ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ ለጉርሱም ወረዳ አስተዳደር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ስር የነበሩት የአኪሾ ጎሳ አባላት በ2011 በሁለቱ ክልሎች መካከል በተደረገው ስምምነት በሶማሌ ክልል ስር በሚገኘው ጉርሱም ተጠቃለዋል።

ባለፈው ዓመት የራሳቸውን የጎሳ መሪ ለመምረጥ ፈልገው በመከልከሉ ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በወረ ሁሜ የጎሳ መሪ ስር ተጠቃለው ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከወረሁሜ ጎሳ መሪ በመውጣት የራሳቸውን መሪ ለመምረጥ እንደሚፈልጉ ኢሰመኮ የማኅበረሰቡ ሽማግሌዎችን ባናገረበት ወቅት ተረድቷል።

ሆኖም የጉርሱም ወረዳ አስተዳደር የአኪሾ ጎሳ በወረ ሁሜ ሥርዓት የሚተዳደር እንደሆነና አዲስ መሪ መምረጥ እንደማይችሉ በመግለጽ ዝግጅቱ እንዳይሄድ ከለከሏቸው። የጎሳ አባላቱ ጉዳዩን ለፋፈን ዞን እንዲሁም ለክልሉ መንግሥት እና ለፀጥታ ቢሮ ያሳወቁ ሲሆን ከክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ መምረጥ ትችላላችሁ የሚል የይሁንታ መልስ እንደተሰጣቸው የጎሳው ሽማግሌዎች ለኢሰመኮ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የወረ ሁሜ የጎሳ መሪ የአኪሾ ጎሳ አባላት አቤቱታቸውን ለእነዚህ የአስተዳደር አካላት ባቀረቡበት ወቅት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው እንዳልተፈቀደላቸውና የጎሳው መሪ ጋር ሂዱ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

የባህላዊ ምርጫው ሥነ ሥርዓት መካሄድ እልባት ሳያገኝ የጎሳው አባላት ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅታቸውን መቀጠላቸውንና ከዚህም ጋር በተያያዘ ለግጭቱ መነሻ ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ መረዳቱን አስፍሯል።

በምርጫው ዕለት ምን ተፈጠረ?

በምርጫው ዕለት መጋቢት 11/2014 ዓ.ም. ቦምባስ ከተማ ቀበሌ 02 የአኪሾ ጎሳ መሪ ለመምረጥ ጥዋት 1 ሰዓት ላይ እስከ 4 ሺህ የሚደርስ ሰው ተሰብስቦ ነበር።

ዝግጅቱ ተጀምሮ ጥዋት 2 ሰዓት አካባቢ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ግለሰቦቹ ስብሰባውን አቋርጠው ይበተኑ በማለቱ አለመግባባት ተፈጥሯል ተብሏል።

ይህም አለመግባባት ተካሮ በተፈጠረው ሁከት በልዩ ኃይሉ አባላት በተተኮሰ ጥይት ስምንት ሰዎች ግንባራቸውን እና ሆዳቸው ላይ በጥይት ተመትተው ለምርጫው በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ መሞታቸውን ኢሰመኮ የሟች ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ በሪፖርቱ አካትቷል።

በተጨማሪም ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ለሰዓታት በፀጥታ ኃይሎች ህክምና እንዳያገኙም ተከልክለውም ነበር ብሏል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በጥይት ሆዳቸው፣ እጃቸው እና እግራቸው ላይ የተመቱ፣ አጥንታቸው የተሰበሩ ተጎጂዎችን ኮሚሽኑ ማየቱን ያሰፈረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያን ይገኙበታል ብሏል፡፡

መጋቢት 12 ዕለት በነበረው የጎሳው አባላት የቀብር ሥነ ሥርዓትም ወቅት፣ ከቀብር በፊት በነበረ የጎሳ ምርጫ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የታጠቁ ግለሰቦች ተኩስ ከፍተዋል ተብሏል።

በዚህም ምግብ እያዘጋጁ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል የእድሜ ባለጸጋ የሆኑ አንዲት ሴት ህይወታቸው ሲያልፍ ሌላ ነፍሰ ጡር ሴት የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በተጨማሪም 11 የአኪሾ ጎሳ አባላት በታጠቁት የጎሳ አባላት በዱላ ተደብድበው የአካል ጉዳት መድረሱም በሪፖርቱ ሰፍሯል።

ኢሰመኮ የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንን ያናገረ ሲሆን የክልሉ ልዩ ኃይል የክልሉ የፀጥታ ቢሮ እና የጉርሱም ወረዳ አስተዳደርን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አለመሳካቱን አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንደከፈለ የተገለጸ ቢሆንም ኢሰመኮ ለተሟላ ፍትሕ የወንጀል ተጠያቂነት ሊረጋጋጥ እንደሚገባም አስምሯል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመው ግድያ ተገቢ አልነበረም ማለታቸውን ሪፖርቱ አስፍሮ፣ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል ማድረጉ ጥሩ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሆኖም "የተሟላ ፍትሕ ለማረጋገጥና ለወደፊትም ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል፤ ስለሆነም በአፋጣኝ የወንጀል ምርመራ ሊጀመር ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ሪፖርቶች በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የጸጥታ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያዎችን እንደፈጸሙና የአካል ጉዳትም እንዳደረሱ ጠቅሶ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል።