የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የዘ ኢኮኖሚስት ዘጋቢን ፈቃድ ሰረዘ

የዘ ኢኮኖሚስት መለያ

የፎቶው ባለመብት, The Economist

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በኢትዮጵያ የዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጣ ዘጋቢ የሆነውን ቶም ጋርድነር ፈቃድ መሰረዙን አስታወቀ።

ዘጋቢው "የሙያ ስነ ምግባርና የሃገሪቱን ህግና መመሪያ መጣሱንም" በመግለፅ ባለስልጣኑ ለፈቃዱ መሰረዝ ምክንያት እንደሆነ በዛሬው ዕለት ግንቦት 5፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ባለስልጣኑ ጥሰቶች ብሎ ያሰፈራቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አልገለጸም።

ባለስልጣኑ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ከዚህ ቀደም ከዘጋቢው ቶም ጋርድነር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች አድርገናል ብሏል።

ባለስልጣኑ ከሳምንታት በፊት ለዘ ኢኮኖሚስት ዘጋቢው ቶም ጋርድነር የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛው በግል የማህበራዊ ሚዲያው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የህወሃት መሪ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር በስልክ ተወያይተዋል የሚል መልዕክት ማስፈሩን ተከትሎ ባለስልጣኑ በሪፖርቱ ላይ በተለይም በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስጠንቅቋል።

ቶም ጋርድነርም ሆነ ዘ ኢኮኖሚስት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

ነገር ግን ይህ እርምጃ በባለስልጣናቱ የሚዲያ ሽፋንን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራ ነው በሚል ትችት ቀርቦበታል።

በባለፈው አመት ጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጋዜጠኞች እና ለተቃዋሚዎች አስቸጋሪ ሁኔታን በመፍጠር ይወቀሳል።

ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች፣ ጅምላ ግድያዎች፣ ደፈራዎች፣ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ተፈፅመውባቸዋል በሚባሉ የጦርነቱ ስፍራዎች ደርሰን መዘገብ ተከልክለናል በሚልም ጋዜጠኞች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ይሰማል።

የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ድርጅት (ሲፒጄ) የጸጥታ ኃይሎች በጦርነት ጊዜ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ለማሰር ተጠቅመዋል ሲል ከቅርብ ወራት በፊት መተቸቱ ይታወሳል።

በወቅቱ በእስር ላይ የዋሉ በርካታ ጋዜጠኞች ከእስር ቢለቀቁም ከአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁለት ጋዜጠኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ናቸው።

ሲፒጄ በተጨማሪም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ናት በሚል ሪፖርት አውጥቷል።

በቅርቡም ድርጅቱ በእስር ላይ ያሉት ደሱ ዱላ እና ቢቂላ አመኑ የተሰኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱና ክሳቸው እንዲቋረጥ ጠይቋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ የሆነው የኦሮሚያ ኒውስ ኔትወርክ ጋዜጠኞቹ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ቢሆንም የታሰሩት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም ደሱ እና ቢቂላ በእስር ቤት እንዳሉና ህገ መንግሥቱን በመፃረር በቀረበባቸው እስከ ሞት የሚያደርስ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ገልጿል።

ከ12 ወራት በፊት በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ የኒውዮርክ ታይምስ ዘጋቢን 'ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ አቅርቧል' በሚል የፕሬስ ፈቃዱን የነጠቀች ሲሆን ይህንን እርምጃም ጋዜጣው 'አምባገነናዊ አካሄድ' እና 'እጅጉን ተስፋ አስቆራጭ' ብሎታል።