በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባለፉት 9 ወራት በደረሰ ድንገተኛ አደጋ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ

የእሳት አደጋ

የፎቶው ባለመብት, FB

ባለፉት 9 ወራት ብቻ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በደረሰ የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለቢቢሲ እንደገለጸው ባለፉት 9 ወራት በመዲናዋ እና አካባቢዋ በደረሱ 377 ድንገተኛ አደጋዎች 511 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በተከሰቱት ድንገተኛ አደጋዎችም የ104 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ154 ሰዎች ላይ ድግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸው፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ድንገተኛ አደጋ የእሳት አደጋ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽኑ መረጃ ከሟቾቹ ውስጥ በእሳት አደጋ የሞቱት 13 ሲሆኑ ሌሎቹ በጎርፍ፣ በኤሌክትሪክ አደጋ፣ ጉድጓድ ውስጥ በመግባት እና በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ በደረሰ አደጋ ሕይወታቸው ያለፉ ናቸው።

አቶ ንጋቱ፣ በመዲናዋ እና አካባቢዋ በደረሰው አደጋ የደረሰው ጉዳት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሬ አሳይቷል ብለዋል።

አደጋዎቹን በመቆጣጠር ሂደት ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቢኖሩም የተጠቀሰው አሃዝ ይህንን እንደማያካትት አክለዋል። ከዚህ ቀደም በአደጋ ሕይወታቸውን ያጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መኖራቸውንም ባለሙያው አስታውሰዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 47 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞቹ በ55 ሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ ማስቀረታቸውንና 3.7 ቢሊየን ብር የሚገመት የንብረት ውድመትን ማዳን ችለዋል ብለዋል።

ለመሆኑ እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ላሉ የእሳት አደጋዎች ምክንያቱ ምንድን ነው?

በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ድንገተኛ አደጋዎች አጋጥመዋል። በዚህም የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ በንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ አዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ የደረሰው የጎርፍ አደጋ የቤተሰብ አባላት ሕይወት አልፏል።

በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ አካባቢ ተለኩሶ በተረሳ ሻማ ሳቢያ የተነሳ የእሳት አደጋ አባትን ከአራት ልጆቹ ጋር በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል።

ቦሌ ቡልቡላ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጋዝ ሲሊንደር ፈንድቶ የ10 እና የ6 ህጻናት ሕይወት አልፏል።

በቅርቡም በአዲስ አበባ ቃሊቲ ኢንደስትሪ መንደር ኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ350 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።

በመዲናዋ እና አካባቢዋ ለተከሰቱ እነዚህ ድንገተኛ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያቶች የከተሞች እያደገ መምጣት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር እንዲሁም የጥንቃቄ ጉድለት ናቸው ይላሉ ባለሙያው።

በከተሞች ያለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር በእሳትና በኤሌክትሪክ የሚገለገሉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ነው ያሉት ባለሙያው፣ ነዋሪው ለመረጃ ቅርብ የሆነ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ቢከተልም ለጥንቃቄ የሚሰጠው ዋጋ ግን አነስተኛ ነው ብለዋል።

በእሳት አደጋ ሕይወታቸው ያለፉ አባትና አራት ልጆቹ

የፎቶው ባለመብት, ABRHAM YIRGA

የምስሉ መግለጫ, በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ አካባቢ ተልኩሶ በተረሳ ሻማ ሳቢያ በተነሳ እሳት የአባትንና የአራት ልጆቹን ሕይወት ቀጥፏል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ካጋጠሙት የእሳት አደጋዎች ውስጥም ከ90 በመቶ በላይ ለሚሆኑት መነሻው የጥንቃቄ ጉድለት ሲሆን 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር የተከሰቱ መሆናቸውን ባለሙያው ጠቅሰዋል።

በጥንቃቄ ጉድለት ከተፈጠሩት ውስጥ ደግሞ ወደ 85.5 በመቶ የሚሆኑት ከኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ወደ ኮሚሽኑ ሪፖርት ያልተደረጉ አደጋዎች እንደሚኖሩ የተናገሩት ባለሙያው፣ እነዚህ አሃዞች ያልተሰሙና ሪፖርት ያልተደረጉ አደጋዎችን አያካትትም ብለዋል። እነዚህ ቢካተቱ በአደጋው የደረሰው ጉዳት ከተጠቀሰው ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የእሳት አደጋን ለመቆጣጠር ምን ያህል ብቁ ነው?

ኮሚሽኑ በመዲናዋ እና አካባቢዋ የሚደርሱ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ፈጥኖ ባለመድረስ እና የሰዎችን ሕይወትና ንብረትን ለማታደግ አስፈላጊ መሳሪያዎች እና ማሽኖች ባለመኖሩ ይተቻል።

ለዚህም በከተማው ውስጥ ቤቶች ተጠጋግተው መሰራት፣ የመንገዶች ምቹ አለመሆን፣ የህንጻዎችና የመኖሪያ ቤቶች ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምቹ ተደርገው አለመሰራታቸው፣ ስለድንገተኛ አደጋዎች በቂ ግንዛቤ አለመኖር አፋጣኝ ምላሽ ላለመስጠቱም እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ይህንኑ ያነሳንላቸው ባለሙያው፣ ኮሚሽኑ በዘጠኝ ቅርንጫፍ ጣቢያዎችና በአንድ ማዕከል እንደሚመራና በእያንዳንዱ ጣቢያ አራት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህ ግን እየተስፋፋ ላለው ከተማ በቂ አይደለም ብለዋል።

ባለሙያው እንዳሉት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንጻ ላይ እሳት ቢነሳ ኮሚሽኑ ይህንን ለመቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ የለውም።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ በመዲናዋ ከሚገኙ ረጃጅም ህንጻዎች አንዱ ሲሆን ከመሬት 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ እና 53 ወለሎች አሉት።

"ህንጻዎች ከፍታቸው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ለእንዲህ ዓይነት አደጋዎች የመጋለጥ እድላቸውን የሚቀንሱበትና የሚቆጣጠሩበት መንገድ መዘርጋት ህንጻዎቹን የሚገነቡት ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና መንግሥት ኃላፊነት ነው" ይላሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ አደጋ ከመድረሱ በፊት መረጃ የሚሰጥና በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተገነባ መሆኑን ይናገራሉ።

ሆኖም በከተማዋ የሚሰሩ የመኖሪያ ህንጻዎች ፣ የንግድ ተቋማት፣ የአደጋ ጊዜ መውጫ እና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ የተገነቡ አለመሆናቸውን ባለሙያው ይተቻሉ።

በህንጻዎቹ ላይ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ የተገጠመላቸው ቢኖሩም አብዛኞቹ አገልግሎት የሚሰጡ እንዳልሆኑና ባለሙያም እንደሌላቸው ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ ከተማ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ለምን የላትም?

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሲገነባ ሁለት ሄሊኮፕተር እንዲያሳርፍ ተደርጎ የተሰራ ቢሆንም አንድም ሄሊኮፕተር የለውም ይላሉ።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በርካታ ጥብቅ ፓርኮች እንዳሉና በመዲናዋም የጉለሌ የእፅዋት ማዕከል እና የእንጦጦ ፓርክ መኖራቸውን ያነሱት ባለሙያው፣ በእነዚህ ፓርኮች እሳት ቢነሳ በከተማ ባሉ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችን ብቻ በመጠቀም ሊጠፋ እንደማይችል ይናገራሉ።

በመሆኑም ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር መኖሩ የግድ ነው ይላሉ።

ባለፉት ዓመታት በርካታ የደን ቃጠሎዎች አጋጥመው አቻ ከሆኑ የአፍሪካ ከተሞች ማለትም ከኬንያ ፣ ደቡብ አፍሪካ ድጋፍ መጠየቁንና በሌሎች አገራት ድጋፍ እሳቱን ለማጥፋት መሞከሩን ባለሙያው አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ጀልባዎች እንደሚያስፈልጉም ጠቁመዋል።

ክልሎች የራሳቸውን የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ለማሟላት ቢሞክሩም ብዙም የተጠናከረ አቅም ስለሌላቸው በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል።

ምንም እንኳን ኢንደስትሪ ፓርኮች ባሉበት አልፎ አልፎ የእሳት አደጋ ማጥፊያዎች በተሻለ ሁኔታ ቢኖሩም፣ በፌደራል ደረጃ የእሳት አደጋ መከለከያና መቆጣጠሪያ ተቋም ቢዋቀር ለሕብረተሰቡ የቀረበ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የእሳት አደጋ ከመድረሱ በፊትና ከደረሰ በኋላ ምን ማድረግ አለብን?

በኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማካተትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት እመቤት ኃይለሚካኤል፣ የእሳት አደጋን ለመከላከል በመኖሪያ መንደርም፣ በተቋምም ደረጃ በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ቀዳሚው ነው ይላሉ።

ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ተቋም ከሚሠራው ሥራ አንጻር አደጋ የሚከላከልበትን ጥንቃቄዎችና እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።

ይህንን ለማድረግ እንዲያስችልም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡና ህንጻዎች ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የሚሰጣቸው መለያ (ኮድ) አለ። በዚህም መሠረት አደጋን የመከላከል ሥራው ህንጻዎች ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር የሚገነቡበትን ጥሬ እቃ ከመምረጥ ይጀምራል።

ምክንያቱም ህንጻዎቹ የሚገነቡበት ጥሬ እቃ እሳትን የመቋቋም አቅማቸው ተመሳሳይ ስለማይሆን ነው።

በመሆኑም ፋብሪካዎች ፣ ባንኮችና ሌሎች ተቋማት የሚገነቡበት ጥሬ እቃ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር የተለያየ መሆን አለበት።

ከዚህም በተጨማሪ ህንጻዎች በሚገነቡበት ጊዜም የእሳት ማጥፊያ ሥርዓት ዝርጋታ፣ የእሳት ማጥፊያ፣ የእሳት ሃይድራንት፣ አደጋ አነፍናፊ መሣሪያዎች [ሴንሰር] መገጠም አለባቸው።

የጭስ፣ የሙቀት፣ የጋዝ እና የጨረር አነፍናፊ መሣሪያዎችን መግጠም፣ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰሩ ማድረግ እና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማዘጋጀትና በየጊዜው መስራታቸውን መከታተል ያስፈልጋል።

የአደጋ ጊዜ መውጫ ቦታዎችን ማለትም በሮችን፣ መንገዶችንና ኮሪደሮችን መገንባት ማዘጋጀት፣ ተንቀሳቃሽ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎችን ማደራጀት እና እሳትን መቋቋም የሚችሉ በሮችን መግጠም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ባለሙያዋ ይመክራሉ።

ይህም ብቻ ሳይሆን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች አዘጋግና አከፋፈታቸውን ለመውጣት አመቺ እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝ ነው።

በመጋዘኖች አሊያም በቤት ውስጥ እቃዎችን ስናስቀምጥ በዓይነት በዓይነታቸው እንዲቀመጡ ማድረግ፣ በእቃዎቹ መካከል ክፍተት እንዲኖረው ማድረግ፣ ተቀጣጣይ ነገሮች ካሉ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲከማቹ ማድረግም ሊደርስ የሚችልን አደጋ በመከላከልና አደጋውን በመቀነስ ረገድ አስተዋጽኦ አለው።

በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለውን ጥግግት ማስቀረት ፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታን በባለሙያ ማከናወንና የጋዝ ሲሊንደር አጠቃቀምን ጥንቃቄ የተሞላበት ማድረግ፣ ያረጁትን መቀየር፣ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን ከተጠቀሙ በኋላ መንቀል፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን በእቃዎች ሥር እና ህጻናት በሚደርሱበት ቦታ አለማስቀመጥ፣ የጋዝ ሲሊንደርን ሙቀት ካለበት ቦታ ማራቅ፣ የማያገለግሉ እቃዎችንና ደረቅ ተቀጣጣይ ነገሮችን ግቢ ውስጥ አለማከማቸት የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው።

አደጋ ከደረሰ በኋላስ ምን መደረግ አለበት?

የእሳት አደጋ ከደረሰ በኋላ እሳቱን በተገኘው ነገር ለማጥፋት ከመሞከር በፊት እሳቱ የተነሳበትን መንስዔ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

በትልልቅ ተቋማት የተገጠሙ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች ህንጻዎቹ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው እሳት ሲከሰት መሣሪያዎቹን በተገቢው መንገድ በባለሙያ በመጠቀም ማጥፋት ወሳኙ እርምጃ ነው።

"የተከሰተ አደጋ ሁሉ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ አይደለም" የሚሉት ባለሙያዋ፣ ሁሉንም እሳት በተመሳሳይ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ ማጥፋት አይቻልም ይላሉ።

የእሳት ማጥፊያ መንገዶች ውሃ፣ ፎም፣ ካርቦንዳኦክሳይድ እና ደረቅ ኬሚካል ዱቄት ናቸው።

እነዚህ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎችን የምንጠቀመውም እንደ የእሳት አደጋው መንስኤ ነው።

ለምሳሌ የነዳጅ ዴፖ፣ የአልኮል መጠጦች፣ የኮስሞቲክስ፣ ዘይት ፣ ቀለም የሚመረቱበትና የሚሸጡበት ቦታ ላይ የተነሳን የእሳት አደጋ በውሃ ለማጥፋት መሞከር እሳቱን ያባብሰዋል።

በመሆኑም ተቀጣጣይ ፈሳሾች ባሉበት ቦታ የተነሳን እሳት ማጥፋት የሚቻለው በፎም ነው። ፎም 90 በመቶው ውሃ ሲሆን 10 በመቶው ውሃ ነው።

ደረቅ ተቀጣጣይ ነገሮች ባሉበት ደግሞ ውሃን መጠቀም አስፈላጊ ነው።

የፋይናንስ ተቋሞች፣ ባንኮች ፣ ቤተ መጽሐፍት ፣ ቤተ መዛግብት፣ ሙዚየም እና የሰነዶች መቀመጫ ቦታዎች ደግሞ በውሃ ቢረጩ ሊበላሹ ስለሚችሉ እሳት ቢነሳ ካርቦንዳ ኦክሳይድን በመጠቀም ማጥፋት ይቻላል።

እሳትን ማጥፋት ያለበት ማን ነው?

የእሳት አደጋ ሲከሰት ማንኛውም ሰው እሳቱን ለማጥፋት መረባረብ አለበት? በምን ዓይነት ደረጃ ላይ ያለ እሳት ነው ያለ ባለሙያ ድጋፍ ሊጠፋ የሚችለው? እሳቱ የተነሳበት ተቋም ወይም ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችስ ምን ማድረግ አለባቸው?

ባለሙያዋ እንደሚሉት ሦስት የእሳት ደረጃዎች አሉ። አንደኛው ጅምር ሲባል ቀሪዎቹ በማደግ ላይ ያለ እና የሞተ እሳት ይባላል።

በመሆኑም በተቋም ወይም በመኖሪያ ቤት ያሉ ሰዎች ሊያጠፉት የሚችሉት ጅምር በተባለው ደረጃ ላይ ያለን እሳት ነው።

እሳቱ በማደግ ላይ ወይም በመስፋፋት ላይ ካለ ግን ሰዎች ቤቱንም ሆነ ህንጻውን ለቀው በመውጣትና በአንድ ላይ በመሰባሰብ ለአደጋ መቆጣጠሪያ ተቋም መደወል ነው የሚጠበቅባቸው።

በዚህ ደረጃ ላይ ያለ እሳት መጥፋት የሚችለው በተሽከርካሪ በታገዘ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ አማካይነት ነው።

ሰዎች እንዲህ ዓይነት አደጋ በሚያጋጥም ጊዜም ወደ ቤቱ የሚገባውን የኦክስጅን መጠን ለመቀነስ እና ወደ ውጭ እሳቱ እንዳይስፋፋ ለማድረግ በርና መስኮት ዘግቶ መውጣትም ይመከራል።

አደጋ በሚከሰትበት ሰዓት ሰዎች በድንጋጤ ይዋጣሉ። ምን አልባት የሚያደርጉት ሊጠፋቸው ይችላል። በዚህም ጊዜ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ።

በዚህ ጊዜ ግን ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ቤታቸውን ወይም ተቋሙን ወዲያውኑ ለቀው በመውጣት ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መደወል እንዳለባቸው ባለሙያዋ ይመክራሉ።

" በአደጋ ጊዜ ለሰው ሕይወት ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት" የሚሉት ባለሙያዋ፣ ተቀጣጣይ ነገሮች የሚለቁት መርዛማ ጋዞች ስላሉ ለእርሱ ሊጋለጡ ስለሚችሉ ቤት ውስጥ የቀረ ሰው ቢኖርም እንኳን ለባለሙያዎች መተው አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዋ ይመክራሉ።

አደጋው የተከሰተበት ቦታ የቀረ ሰው ካለም መረጃዎች በመስጠት፣ የቤቱን ወይም የተቋሙን መግቢያ መውጫ በማመላከት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ማገዝ እንደሚገባም ባለሙያዋ ተናግረዋል።

አሁን አሁን በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚገነቡ ህንጻዎች እና የመኖሪያ መንደሮች እየተበራከቱ ነው። ይሁን እንጂ በርካታ ማሕበረሰብ የሚኖርባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ መንግሥት ህንጻዎች ሲገነቡ ለደህንነት ጥንቃቄ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ከግምት አያስገቡም።

አብዛኞቹ የአደጋ መውጫ ጊዜ መውጫ ኮሪደርና በሮች የሏቸውም። የተገጠመላቸው የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎችም እንዲሁ የተገጠመላቸው አይደሉም።

በተለይ ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች የተጠጋጉና አደጋን ለመቆጣጠር የሚያመቹ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የላቸውም።

አንድ ህንጻ ሲገነባ ከዲዛይኑ ጀምሮ ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ደንቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሕግ ቢኖርም አፈጻፀም ላይ ግን ችግር እንዳለ ባለሙያዋ ይናገራሉ። ይህም በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንዲባባስ አድርጎታል።

አንዳንድ ህንጻዎችና ተቋማት ቁሳቁሶቹን ለደንቡ ቢያሟሉም ባለሙያ የሌላቸውና በየጊዜው ፍተሻ እንደማይደረግላቸውም ባለሙያዋ ተችተዋል።

አሁን ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተሳሰር ይህንን ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ ቢሆንም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ባለሙያዋ አሳስበዋል።