በትናንቱ ጎርፍ በመካኒሳ ሴሚናሪ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Fana BC
ትናንት በአዲስ አበባ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተለምዶ መካነ እየሱስ ሴሚናሪ ተብሎ በሚጠራው ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና አንዲት ሴት የገበችበት አለመታወቁ ተገለጸ።
የመካነ እየሱስ ማነጅመንት እና ሊደርሺፕ ኮሌጅ የሕግ እና ሚዲያ ኃላፊ አቶ አሴር ሰይፉ ከኮሌጁ አቅራቢያ የሚገኘው የመካኒሳ ወንዝ ሞልቶ ወደ 10 ሰዓት አካባቢ የሴሚናሪውን አጥር አፍርሶ መግባቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ መካነ እየሱስ ሴሚናሪ የሚገኝበት ጀርመን አደባባይን ጨምሮ በአስኮ፣ አደይ አበባ እና ጎልፍ ክለብ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማጋጠሙን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በበኩሉ የአዲስ አበበ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍሰሃን በመጥቀስ በጎርፍ አደጋው የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዘግቧል።
የመካነ እየሱስ ማነጅመንት እና ሊደርሺፕ ኮሌጅ የሕግ እና ሚዲያ ኃላፊ አቶ አሴር ሰይፉ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች የጎርፍ አደጋው ሲከሰት በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንደነበሩ ተናግረው፤ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው የጠፋችውን እንዲት ሴት ለማግኘት ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አደጋው ያጋጠመው በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባሉ የመምህራን እና የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መሆኑን እና አቅም የነበራቸው ሰዎች በቤቶች ጣሪያ ላይ በመውጣት ሕይወታቸውን መታደጋቸውን አቶ አሴር ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ አሴር በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደ 300 የሚጠጉ ተማሪዎች በተማሪ መኖሪያ ዶርም ውስጥ እንደሚኖሩ አስታውሰው፤ የተማሪዎቹ መኖሪያ ሕንጻ ከፍታ ስላለው በተማሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጨምረው አስረድተዋል።
በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በቅጥር ግቢ ውስጥ ቆመው የነበሩ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ በሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ አሴር ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም በቅጥር ግቢው አካባቢ ጎርፍ ተከስቶ እንደሚያውቅ አስታውሰው፤ "ይህ አደጋ ግን እጅጉን የከፋ እና የሰው ሕይወት የቀጠፈ ነው" ብለዋል።

የመካነ እየሱስ ማነጅመንት እና ሊደርሺፕ ኮሌጅ በአስተዳደር እና ሥራ አመራር ስልጠናዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የተቋቋመው እና እውቅናን ያተረፈው መካነ እየሱስ ጃዝ ሙዚቃ ትምህርት ቤትም የኮሌጁ አንድ አካል ነው።

አሁንም የአየር ትንበያ መረጃዎች በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለዉ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ትንበያ ሰጥተዋል። በዚህም ነዋሪው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት እና ከተከሰተ በኋላ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይመከራል።












