ቀራኒዮ አካባቢ በተከሰተ የእሳት አደጋ አባት ከአራት ልጆቻቸው ጋር ሕይወታቸውን አጡ

የፎቶው ባለመብት, Abrham Yirga
አርብ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ. ም. በቀራኒዮ አካባቢ ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ በተፈጠረ የእሳት አደጋ ምክንያት አንድ አባት ከአራት ልጆቻቸው ጋር ሕይወታቸውን እንዳጡ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገለጹ።
በአደጋው ሳቢያ አራት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን አጥተው ከ10 ወር ልጃቸው ጋር በሕይወት የተረፉት የወ/ሮ አምሳል ይርጋ ወንድም የሆኑት አቶ አብርሃም ይርጋ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ከአንድ ቤተሰብ አምስት ሰዎች በአደጋው ሞተዋል።
የእሳት አደጋው በተከሰተበት ዕለት በኮልፌ ቀራኒዮ መብራት እንዳልነበረ እና ቤተሰቡ ሻማ አብርቶ እንዳመሸ አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
"[እህቴ] በከሰል ምግብ እያበሰለች ነበር። ባለቤቷ ሶፋ ላይ ከአንድ ልጃቸው ጋር ጋደም ብሎ ነበር። አሁን በሕይወት የተረፈችውን ልጅ ልታጠባ ስትገባ እንቅልፍ ወሰዳት" ሲሉ የተፈጠረውን ያስታውሳሉ።
እናት ልጃቸውን ለማጥባት ወደ ጓዳ ገብተው እንቅልፍ አሸልቧቸው ሳለ እሳቱ እንደተነሳ ወንድም አቶ አብረሃም ይርጋ ተናግረዋል።
ከዚያም ጎረቤት ተረባርቦ እናትና የ10 ወር ልጃቸውን ማትረፍ ቢችልም አባትና የአራቱን ልጆቻቸውን ሕይወት ግን ማዳን ሳይቻል ቀርቷል።
በዚህም አደጋ አባት አቶ ጊዜ ብሩ እና ሴት ልጆቻቸው ኑሃሚን፣ ናርዶስ፣ ልደት እና ጽዮን ሕይወታቸው አልፏል።
"ድንገት ከእንቅልፏ ስትነሳ እሳት ተነስቶ ነበር። [እያጠባቻት የነበረችውን] ልጇን አፋፍሳ ይዛ ወደ ውጭ ወጥታ ጮኸች። ጎረቤት ደርሶ እሷን አስጣላት። ሌሎቹን ማዳን ግን አልተቻለም" ብለዋል።
ወ/ሮ አምሳል ባለቤታቸውንና አራት ልጆቻቸውን ለማትረፍ ወደ ቤት እንደተጣሩ የገለጹት ወንድማቸው ሆኖም ግን ባለቤታቸው "ብጠራውም አልነቃም" ማለታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ15፣ የ11፣ የ8 እና የ6 ዓመት ሴቶች ልጆቻቸው በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ቤታቸውም በቃጠሎው ወድሟል።
የአባትየውና የአራቱ ልጆች ሥርዓተ ቀብር ታኅሣሥ 16/ 2014 ዓ. ም. በወይበላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ፤ ባለፈው አርብ በተከሰተው የእሳት አደጋ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ አረጋግጠው፤ "የአደጋው መንስኤ ገና እየተጣራ ነው" በማለት ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጨምረውም አደጋው የደረሰባቸው አባትና ልጆቻቸው ሆስፒታል የደረሱት በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው አባት አቶ ጊዜ ብሩ የፒክአፕ መኪና አሽከርካሪ እንደነበሩና በዚሁ ሥራቸው ቤተሰባቸውን ከእጅ ወደ አፍ በነበረ ሁኔታ ያስተዳድሩ እንደነበር ተናግሯል።
"ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው። ግን ከቤተሰቡ አልፎ እኛን ሁሉ ይረዳን ነበር። የትም ቦታ ያለው ስም ጥሩ ነው። ሰፈር ውስጥ ስለ እሱ ማንም መጥፎ አያወራም" በማለት የእህቱን ባለቤት አቶ አብረሃም ገልጸዋል።
ከአደጋው የተረፈችው እህታቸው እና የ10 ወር ልጇ አሁን ላይ ደኅና እንደሆኑ ጠቅሰው ነገር ግን ባለቤቷንና አራት ልጆቿን አጥታ ባዶ ቤት በመቅረቷ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ በሐዘን አስረድተዋል።
እህታቸው ያለችበትን ሁኔታ ሲገልጹም "በአንድ ቀን አምስት ሬሳ መቅበር ከባድ ነው። የት እንደተቀበሩ ራሱ ያወቀችው ዛሬ ነው" ብለዋል።












