የቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት፣ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሦስት ወንድሞና አራት ዘመዶቻቸው እንዴት ተገደሉ?

የሟች ቤተሰቦች ከተቃጠለው ቤታቸው ፊት ለፊት የሟች ቤተሰቦቻቸውን ምስል ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Nonno Benja Communication

የምስሉ መግለጫ, የሟች ቤተሰቦች ከተቃጠለው ቤታቸው ፊት ለፊት የሟች ቤተሰቦቻቸውን ምስል ይዘው

የቀድሞው ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሦስት ወንድሞች እና አራት ዘመዶቻቸው፣ በመኖሪያ አካባቢያቸው በተፈፀመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ግድያው ባለፈው ሳምንት አርብ ጠዋት፣ በቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ የትውልድ ቦታ በጅማ ዞን ኖኖ ቤንጃ ወረዳ፣ ኮንቺ ከበሌ የተፈፀመ ሲሆን በአጠቃላይ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ስምንት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ተጎድተው በሕይወት መትረፋቸውን እና በአቅራብያ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከተገደሉት ስምንት ሰዎች መካከል ሰባቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የቅርብ ቤተሰቦች ሲሆኑ አንደኛው ጎረቤት መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆናቸው አዛውንት የሚገኙበት ሲሆን በተጨማሪም እናትና አንዲት የ25 ዓመት ሴት ልጅ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ግድያው "ታስቦበት የተፈፀመ " መሆኑን ቤተሰቡ አንደሚያምን የተገለፀ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ ግድያውን ለመፈፀም ጥይት እና ስለት ነገሮችን መጠቀማቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

በግድያው መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው እና ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር የተባለው ቡድን የተወነጀለ ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድኑ ስለግድያው ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ-ሸኔ የሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ከህወሓት ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማደረግ ከስምምነት ላይ መድረሱ የሚታወስ ሲሆን ሁለቱም በሽብር ቡድንነት መፈረጃቸው ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት ከተፈፀመው ግድያ በተጨማሪ በጥቃት አድራሾቹ ቢያንስ 17 ቤቶች እንዲሁም እህል መቃጠሉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በአካባቢው የቀሩ የቤተሰብ አባላት አሁንም ስጋት እንዳለባቸው እና የቅርብ ዘመዶቻቸውን ሐዘን ተረጋግተው መቀመጥ አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

አርብ ታኅሣሥ15 የሆነው ምንድን ነው?

ግድያው የተፈፀመው አርብ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 አስከ 4 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ መንደር ውስጥ መሆኑን የኖኖ ቤንጃ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኩመራ ዲጋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሦስቱ የተገደሉት የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት የአቶ አለማየሁ አቶምሳ ታላቅ ወንድሞች መሆናቸው እና የበርካታ ልጆች አባቶች እንደነበሩም ጨምረው አስረድተዋል።

አቶ ኩመራ አክለውም "የተገኘው የስምንት ሰዎች ሬሳ ነው፤ ሁለት ሰዎች የሕክምና ተቋም ተወስደዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ ሦስት ወንድማማቾች መካከል አቶ ሙላቱ አቶምሳ፣ እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን የዘጠኝ ልጆች አባት ነበሩ።

አቶ ጢንቲ አቶምሳ ከ70 ዓመት በላይ የሚሆናቸው ሲሆን የስምንት ልጆች አባት ናቸው።

እንዲሁም አቶ አደባ አቶምሳ ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜያቸው የተገመተ ሲሆን፣ የስምንት ልጆች አባት መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተቃጠለ እህል ክምር

የፎቶው ባለመብት, Nonno Benja Communication

የምስሉ መግለጫ, የተቃጠለ እህል ክምር

የስምንቱ ሟቾች ቀብር አርብ ምሽት 1፡30 ላይ መፈፀሙን የወረዳው አስተዳዳሪ እና ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስለተፈፀመው ጥቃት የተጠየቁት የአቶ ጢንቲ ልጅ፣ አቶ አዳነ "ሰዉ ሲጠነቀቅ፤ ሲፈራም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ይፈፀማል ብሎ አንድም የጠበቀ አልነበረም" ብለዋል።

"አባቴ እና ታላቅ ወንድሙ በአንድ ቦታ ነው በአራት ጥይት የተገደሉት፤ የአገር ሽማግሌ ነበር፤ ሰውን የሚያስታርቅ፤ ማኅበረሰቡ ውስጥ የተከበረ ሰው ነበረ" ሲሉ አክለዋል።

ግድያውን የፈፀሙት ታጣቂዎች እንደሆኑ ከቤተሰብ መስማታቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አዲሱ አደባም፣ አባታቸው አቶ አደባ አቶምሳ በታጣቂዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ቤትም ተቃጥሏል፤ ግድያውም በሚኖሩበት ቀዬ ነው የተፈፀመው፤ አቶ ሙላቱን እና ጢንቲ አቶምሳን በአንድ ቤት ውስጥ ነው የገደሏቸው። አባቴ በቤቱ ብቻውን ነው የሞተው፤ መረጃ ሰብሰብው ግድያውን መፈፀማቸውን ሰምተናል። ዝም ብለው አይደለም ዘመድ የሆኑትን መርጠው አንድ ቤተሰብን የማጽዳት እርምጃ የወሰዱት።"

". . . በተለይ የሚያሳዝነው ነገር አቶ ሙላቱ አቶምሳ የተባሉት ዓይናቸው እንኳ ማየት የማይችል፤ ደካማ ሽማግሌ ነበሩ። በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው የተገደሉት" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ከሦስቱ ወንድማማቾች በተጨማሪ በታጣቂዎቹ ከተገደሉት አምስት ሰዎች መካከል አራቱ የአቶ ሙላቱ አቶምሳ ዘመዶች መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ከተፈፀመው ግድያ ውጪ በአሁን ጊዜ በሕይወት የተረፉ የቤተሰብ አባላት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳሉም ጨምረው አስረድተዋል።

"የዘመዶቻቸውን ሐዘን እየተቀመጡ አይደለም፤ ማታ ጫካ ነው ያደሩት፤ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው ያሉት፤ የሞተውማ ሞቷል ለቋሚዎቹ ነው ከፍተኛ ስጋት ያለን" ሲሉ አቶ አዳነ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ቤተሰቡ ዒላማ ተደርጓል?

የሟች ቤተሰቦች የቤተሰቦቻቸው አባላት ዒላማ ተደርገው እንደተገደሉ የሚያምኑ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፣ የወረዳው አስተዳዳሪ በበኩላቸው ይህ ግድያ "እንደ አጋጣሚ የተፈፀመ አይደለም" ይላሉ።

"ባለን የተጠናከረ መረጃ መሰረት ሆን ተብሎ፣ በዚያ በኩል ተገብቶ ጥቃቱ ተፈፀመ፤ ከዚያ በኋላ ቆመውም ወደ ሌላ ሰው አልተኮሱም፤ ሌላ ቤትም አላቀጠሉም፤ በአንድ መንደር ውስጥ ያሉ ቤቶችን እያቃጠሉ ሰላማዊ ዜጎችን እየገደሉ በአጭር ደቂቃ ውስጥ ነው ይህንን ድርጊት ፈጽመው የተመለሱት፤ ተፈልገው ነው ባሉበት የተገደሉት" ሲሉ አቶ ኩመራ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ግድያው ሲፈፀም የአካባቢ ታጣቂዎች በስፍራው ያልነበሩ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ግለሰቦቹም በመኖሩያ ቤታቸው እና አካባቢያቸው እንደነበሩ ተናግረዋል።

ሌላው የቤተሰብ አባልም ከጥቃት አድራሾቹ ፊት ለፊት አንድ ግለሰብ ከፊታቸው እየሄደ አቅጣጫ ያሳይ እንደነበር እንደሰሙ መስክረዋል።

"የእኛ ዘመዶች ያልሆነ ቤት የተቃጠለው በጣም ጥቂት ነው። ሲጀመር ከእኛ ዘመድ ነው ቤት ማቃጠል የጀመሩት፤ ስለዚህ ተቀነባብሮ የተፈፀመ ነው" ይላሉ አቶ አዳነ ለቢቢሲ ስለ ጥቃቱ ሲያስረዱ።

ጨምረውም "ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል እንጂ ሌላ አይደለም ይህንን ግድያ የፈፀመው። ይህ እኮ በቀን ነው የተፈፀመው" በማለት ቤተሰቦቻቸው "እንደ ከብት መገደላቸውን" ይናገራሉ።

ሌላው ያነጋገርናቸው የቤተሰብ አባልም ግድያው በታጣቂዎቹ በጥይት እንዲሁም በስለት መፈፀሙን ይናገራሉ።

የወረዳው ነዋሪዎች ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱን በመቃወም ሰልፍ አድርገው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Nonno Benja Communication

የምስሉ መግለጫ, የወረዳው ነዋሪዎች ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱን በመቃወም ሰልፍ አድርገው ነበር

የጥቃቱ ምክንያቱ ምንድን ነው?

የኮንቺ ቀበሌ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋማ ቦኔያ ከተባለ ወረዳ ጋር ትዋሰናለች።

እንደ ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳዳሪ ገለጻ እነዚህ ታጣቂዎች በአጎራባች ዞን ያደ ሁንዳ ቀበሌ ሰፍረው ይገኛሉ።

ታጣቂዎቹ በተለያየ ጊዜም ወደ ኮንቺ ቀበሌ ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር። የሟች ቤተሰቦች እንደሚናገሩት ግድያው ከመፈፀሙ ከሁለት ቀን በፊት ታጣቂዎች ወደ ኮንቺ ቀበሌ መጥተው ተኩስ ከፈተው ነበር።

ከዚያ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎች ውስጥ ሁለቱን መግደላቸውን ይናገራሉ።

በቀጣይ ታጣቂዎቹ ኃይል ጨምረው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሌሉበት ሰዓት በመምጣት ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የኮንቺ ቀበሌ ሊቀመንበር የአቶ አለማየሁ ዘመድ መሆናቸውን በማንሳት ለጥቃት ዒላማ ሊሆኑ አንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ይናገራሉ።

እንዲሁም የአንድ የሟች ልጅ የአካባቢ ሚሊሻ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል። አክለውም "ቂም መወጫ ይመስላል. . . አንተን ካጣንህ ቤተሰብህን አናጣም" በሚል የተፈፀመ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ነጻነት ጦር፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥት መዋቅር አባላትን፣ የቀበሌ ሊቀመንበር፣ ሚሊሻ እና የመንግሥት አመራሮችን፣ ፖሊስን ዒላማ በማድረግ ጥቃት መፈፀማቸው ይታወሳል።

አቶ አለማየሁ የኦሮሚያ ክልልን ሲያስተዳድሩ ስለነበር ቤተሰቡ በዚህ የተነሳ ዒላማ ተደርጎ ይሆናል ብለው ያምኑ እንደሆን የተጠየቁት የቤተሰብ አባል 'ሊሆን ይችላል' ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ይናገራሉ።

ነገር ግን አቶ አለማየሁ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ቤተሰቦቻቸው "የተለየ የተጠቀሙት ነገር" እንደሌለ ይናገራሉ።

የወረዳው አስተዳዳሪ በበኩላቸው የኮንቺ ቀበሌ 'ታጣቂዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ' የጥቃት ዒላማ እንደሆነች ገልፀዋል።

የታጣቂዎች እንቅስቃሴ

የኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ግን ወደ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ እና ምዕራብ ሸዋ በስፋት መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ይስተዋላል።

ይህ የታጣቂ ቡድን ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚፈፀሙ ግድያዎች በነዋሪዎች፣ በመንግሥት እና በሰብዓዊ መብት ተቋማት ይወነጀላል።

ነገር ግን ቡድኑ ይህንን ውንጀላ አይቀበልም።

ስለ ታጣቂዎቹ ማንነት የተጠየቁት የወረዳው አስተዳዳሪ "በምሥራቅ ወለጋ ከሸኔ ውጪ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የለም" ሲሉ ይመልሳሉ።

ባለፈው ዓመት በጅማ ዞን በሊሙ ኮሳ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ነዋሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ጦርን መወንጀላቸው ይታወሳል።

የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አለማየሁ አቶምሳ

የፎቶው ባለመብት, Addis Fortune

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አለማየሁ አቶምሳ

ከባለፈው አርብ ግድያ በፊት ጥር 2013 ዓ.ም ታጣቂዎች ወደ ኖኖ ቤንጃ ወረዳ ለማለፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው እንደነበር ይናገራሉ።

"እዚህ ወረዳ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤ ተንቀሳቅሰውም አያውቁም፤ መቀመጫቸውም ምሥራቅ ወለጋ ዞን ቦነያ ቡሼ ወረዳ በማድረግ ነው እርምጃ ወስደው የተመለሱት" ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ ያስረዳሉ።

የኖኖ ቤንጃ ወረዳ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ካሉ የቢሎ ቤሾ እና ዋማሃ ገሎ ወረዳዎች ጋር ትዋሰናለች።

አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከ1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ለአራት ዓመታት ያህል አቶ አባዱላ ገመዳን በመተካት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ አለማየሁ ስልጣናቸውን በሕመም ምክንያት መልቀቃቸው በተገለፀ በሁለተኛው ሳምንት ከዚህ ዓመት በሞት መለየታቸው ይታወሳል።