በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ የመጨረሻው ዋና ተፈላጊ ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ

ፕሮታይስ ኤምፒራንያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ የፕሮታይስ ኤምፒራንያ እንደሆነ በታመነው መቃብር ላይ በተደረገው ቁፋሮ በ2006 ሕይወቱ ማለፉን ማረጋገጥ ተችሏል።

እ.ኤ.አ. በ 1994 በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተከሰሰው እና በወንጀሉ ከሚፈለጉ ሰዎች የመጨረሻው ዋና ተፈላጊ ግለሰብ በሽሽት በኖረበት ዚምባብዌ ሕይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።

ፕሮታይስ ኤምፒራንያ በጭፍጨፋው ወቅት የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት የጥበቃ ኃላፊ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አጋቴ ኡዊሊንጊማና እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥቷል በሚል ክስ ይቀርብበት ነበር።

እንዲሁም ወታደሮቹ ጠቅላይ ሚኒስትሯን የሚጠብቁ 10 የቤልጂየም ዜጋ የሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎችን በመግደልም ተከሶ ነበር።

ለዓመታት የዘለቀው የመርማሪዎች ፍለጋ ወደ ዚምባብዌ ያመራ ሲሆን፣ በቅርቡ የግለሰቡ እንደሆነ በታመነው መቃብር ላይ በተደረገው ቁፋሮ ሕይወቱ እአአ 2006 ላይ ማለፉን ማረጋገጥ ችለዋል።

መርማሪዎቹ ጨምረውም ኤምፒራንያን ከ12 ዓመታት በላይ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በሚደረግበት ወቅት ስሙን እየቀያየረ በሽሽት መኖሩንም ደርሰውበታል።

በ100 ቀናት ውስጥ ወደ 800,000 የሚጠጉ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች በሁቱ ጽንፈኞች የተገደሉበት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማግስት ግለሰቡ ወደ ካሜሩን ሸሸ።

በወቅቱ በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ተሳትፈዋል ተብለው የተከሰሱት ግለሰቦች በድንበር ወደ ኮንኮ በመሸሽ ኤፍዲኤልአር በመባል የሚታወቅ አማፂ ቡድን መሥርተው ነበር።

ኤምፒራንያ በ1998 ከዚምባብዌ ጦር ጋር በመሆን የሚዋጋውን ብርጌድ በማዘዝ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ አገራትን ባሳተፈው ግጭት ውስጥ ተቀላቅሎም ነበር።

ስሙን ወደ አሊን ሂርዋ በመቀየር "ኮማንደር አላይን" በመባል ይታወቅ እንደነበር ብሎም በዚምባብዌ መኮንኖች ዘንድም እጅግ የተከበረ እንደነበር መርማሪዎቹ አረጋግጠዋል።

እ.ኤ.አ. በ2002 በዘር ማጥፋት ወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑትን ለፍርድ ለማቅረብ በተቋቋመው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ፣ ማንነቱ ለህዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ በዚምባብዌ ዋና ከተማ ሃራሬ መጠጊያ ያደረጉለት የዚምባብዌ አጋሮቹ መሆናቸውም ታውቋል።

ግለሰቡ በስምንት ወንጀሎች ክስ የቀረበበት ሲሆን በፕሬዘዳንቱ ጠባቂዎች የተፈጸሙ የዘር ማጥፋት፣ ግድያ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን በማስተማር፣ በመቆጣጠር፣ በማበረታታት እና በማገዝ የሚሉት ይገኙበታል።

ኤምፒራንያን አድኖ ለመያዝ የተካሄደውን ምርመራ ያደረገው በሩዋንዳ እና ዩጎዝላቪያ ከፍተኛ የጦር ወንጀል ጉዳዮችን የሚከታተለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው ተቋም ነው።

''በወንጀሉ ሰለባ ለሆኑት ግለሰቦች ኤምፒሪያንያ እጅግ የሚያስፈራ እና ጨካኝ ግለሰብ ነበር'' ሲል ነበር የምርመራ ቡድኑ የገለጸው።

''ሞቱን ማረጋገጥ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ እንደማይችል ማወቅ መፅናናትን ይሰጣል" ሲሉም ተመድ ያቋቋመው የዩጎዝላቪያ እና የሩዋንዳን ጭፍጨፋ የሚመለከተው ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ የሆኑት ሰርጌ ብራሜርዝ ተናግረዋል።

ግለሰቡ በዚምባብዌ በቆየባቸው አራት ዓመታት ከባለቤቱ እህት ጋር የንግድ ሥራ ይሠራ የነበረ ሲሆን እስከ ህልፈቱ ድረስ ከኤፍኤልዲአር ጋር ግንኙነት ነበረው። ጄምስ ካኩሌ በሚል ስምም የዩጋንዳ ፓስፖርት ነበረው።

እንዲሁም ባለቤቱ እና ሴት ልጆቹ ኑሯቸውን በእንግሊዝ ቢያደርጉም ሃራሬ በመሄድ ጎብኝተውት እንደነበረም ታውቋል።

እ.ኤ.አ. በ2006 በሳምባ ነቀርሳ ሕመም ተይዞ በጠና ሲታመም 50 ዓመቱ ገደማ የነበረ ሲሆን ኤንዱሜ ሳምቡ በሚል ስም ይጠቀም ነበር።

ይህ ስምም ከሃራሬ ውጭ ባለው መቃብሩ ላይ የሰፈረው ስም ሆኗል።