ሶስት ሴቶችን የገደለው ወንጀለኛ ማረሚያ ቤት ውስጥ ማግባት እንደሚፈልግ ገለጸ

ሌቪ ቤልትፊልድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሌቪ ቤልትፊልድ

ሶስት ሴቶችን ገድሎ አንደኛዋን ያቆሰለው ወንጀለኛ ሌቪ ቤልትፊልድ የትዳር አጋር እንዳጨና ማረሚያ ቤት ውስጥ ሰርጉን መደገስ እንደሚፈልግ የእንግሊዝ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የ53 ዓመቱ ሌቪ ትዳሩን ለመመስረት የከተማዋን አስተዳዳሪ የመጨረሻ ይሁንታ ማግኘት አለበት።

ወንጀለኛው ማርሻ ማኮኔል፣ ኤምሊ ዴላግራንዴ እና ሚሊ ዶውለር የተባሉ ሴቶችን በጭካኔ በመግደል ጥፋተኛ ተብሎ ሁለት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

የቀድሞው የፍትህ ሚኒስቴር ሮበርት በክላንድ ዘ ሰን ለተባለው ጋዜጣ ሲናገሩ ሰርግ የመደገስ ሀሳቡ ''ለማመን የሚከብድ ነው'' ብለዋል።

''የ13 ዓመቷ ሚሊ የሰርግ ቀኗን ማየት ሳትችል ነው የገደላት። እሱ ደግሞ ሰርግ ለመደገስ ማሰቡ ትክክል አይመስለኝም'' ብለዋል።

ወንጀለኛው ከሁለት ዓመታት በፊት በጽሁፍ ታገኘው የነበረችው ግለሰብ ጋር እንደተቀራረቡና በተደጋጋሚ ትጎበኘው እንደነበር ዘ ሰን ዘግቧል።

ከሰሞኑ ደግሞ ልትጎበኘው ስትመጣ ተንበርክኮ የታገቢኛለሽ ጥያቄውን ማቅረቡ ተዘግቧል።

የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ''ሰርጉን ለመደገስ ይፋዊ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊት በምንሰራበት አሰራር እየተጠና ነው'' ብለዋል።

ሌቪ ቤልትፊልድ በፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ጥፋተኛ መባሉን ተከትሎ ከ14 ዓመታት በፊት የእድሜ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

በማረሚያ ቤት በነበረበት ወቅት ደግሞ የ13 ዓመቷ ሚሊን በመግደል በድጋሚ ፍርድ ቤት ቆሞ ነበር። ሚሊ ዶውለር ከትምህርት ቤት ወደ ቤቷ በመሄድ ላይ በነበረችበት ወቅት 2002 ላይ ነበር ታፍና የደረሰችበት ያልታወቀው።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ 2011 ላይ ሌቪ በድጋሚ ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ተከትሎ ተጨማሪ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ሌቪ ቤልትፊልድ በአንድ የምሽት ክለብ ውስጥ በጥበቃነት ያገለግል የነበረ ሲሆን ከ5 የተለያዩ ሴቶች 11 ልጆችን መውለዱን ዘ ሰን ዘግቧል።

ከሌቪ ጋር አብረው ይሰሩ የነበሩ ባልደረቦቹን ያነጋገረው መርማሪ ሲናገር ሁሉም መጀመሪያ አካባቢ በጣም ተጫዋችና አዝናኝ እንደሆነ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ሁሉንም ሰው መቆጣጠር የሚፈልግና ጨካኝ እንደሆነ መናገራቸውን ገልጸ ነበር።