በአሜሪካ ከታራሚ ጋር ተያይዛ የጠፋችው የማረሚያ ቤት ፖሊስ ራሷን በጥይት አጠፋች

ታራሚ ኬሲ ዋይት ( በስተግራ) እና የማረሚያ ቤት ፖሊስ ቪኪይ ዋይት

የፎቶው ባለመብት, LAUDERDALE COUNTY SHERIFF'S OFFICE

በግድያ ወንጀል ከተጠረጠረ ታራሚ ጋር ጠፍታ የነበረችው የማረሚያ ቤት ፖሊስ ራሷን ተኩሳ መግደሏን ፖሊስ አስታወቀ።

ፖሊስ እንዳለው የ58 ዓመቷ ቪኪ ዋይት እና የ38 ዓመቱ ታራሚው ኬሲ ዋይት፣ በፖሊስ ክትትል በኢንዲያና ከተያዙ በኋላ ቪኪ ራሷ ላይ ተኩሳ ሆስፒታል ከገባች በኋላ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

ሁለቱ ግለሰቦች በሎዴርዴል ካውንቲ ከሚገኝ እስር ቤት ተያይዘው የጠፉት ከአስራ አንድ ቀናት በፊት ሲሆን ግለሰቦቹ የፍቅር ግንኙነት እንዳላቸው ይታመናል።

እንደ ባለሥልጣናት ከሆነ ታራሚውና ፖሊሷ ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት ታራሚውን ወደ ቦጋስ ለአዕምሮ ጤና ግምገማ ስትወስደው ነበር።

ያን ዕለት ቪኪ ጡረታ ለመውጣት የመጨረሻ የሥራ ቀኗ ነበር ።

ቪክ በቅርቡ ቤቷን የሸጠች ሲሆን ቀሪ ጊዜዋን በባህር ዳርቻዎች እየተዝናናች ለማሳለፍ እንዳቀደች ለሥራ ባልደረቦቿ ተናግራ ነበር።

ሰኞ ዕለት የቫንደርበርግ ካውንቲ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ቪኪ ዋይት በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ጊዜ ራሷ ላይ ከተኮሰች በኋላ መሞቷን አረጋግጧል።

ከአስክሬን ምርመራ በኋላ ዛሬ አማሟቷን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ሎዴርዴል ካውንቲ ሸሪፍ ሪክ ሲንግልተን ቀደም ብሎ እንዳስታወቁት ፖሊስ ጥንዶቹን በኢንዲያና፣ ኢቫንስቪል ሲከታተላቸው ጥንዶቹ የነበሩበት መኪና የተጋጨ ሲሆን በቁጥጥር ሥር የዋሉትም እዚያው የተጋጩበት ቦታ ነው።

" ዛሬ አደገኛ የሆነ ሰው ይዘናል ። ከዚህ በኋላ በፍፁም የቀን ብርሃን አያይም" ብለዋል ሪክ ሲንግልተን።

የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት እንዳለው ሁለቱ ግለሰቦች ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት አርብ ዕለት የአላባማ ታርጋ ቁጥር ያለው ፎርድ ኤጂ መኪና እያሽከረከሩ ነበር።

ሰኞ ዕለት ሼሪፍ ሲንግልተን፣ ኬሲ ዋይትን "በጣም አደገኛ ነው" ሲል የገለጹት ሲሆን ሕግ አስፈጻሚዎች ምንም አይነት እድል እንዳይሰጡ ተናግረው ነበር።

ቪኪ ዋይት ግን የማረሚያ ቤት ፖሊስ ሆና ስታገለግል ምንም ዓይነት ጥፋት ሰርታ የማታውቅ ታማኝ ሠራተኛ ነበረች።

"ቪኪ በሕይወቴ የማምናት ሰው ነበረች፤ ጠንካራ ሠራተኛም ጭምር። ለዚያም ነው ሁኔታው ያስደነገጠን" ሲሉ የላውዴርዴል ካውንቲ አቃቤ ሕግ ክሪስ ኮኖሊ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሼሪፍ ሲንግልተን እንዳሉት የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪ ፖሊሷ ቪክ፣ በሥራ ክፍሏ ለ25 ዓመታት አገልግላለች።

የእርምት ረዳት ዳሬክተርም ስትሆን እስረኞችን ወደ ፍርድ ቤት ማመላለስ ከኃላፊነቶቿ መካከል አንዱ ነበር።

የ38 ዓመቱ ጎልማሳ ኬሲ እአአ በ2020 የ58 ዓመቷ ኮኒ ሪጂዌይን በስለት በመግደል በሁለት ከባድ የግድያ ወንጀሎች እንደተከሰሰ የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት ገልጿል።

እአአ በ2015 ማጭበርበርን እና የተሽከርካሪ ስርቆት ጨምሮ በተከታታይ የወንጀል ድርጊቶች በቀረበበት ክስ በእስር ላይ እንደነበር አስታውቋል።

ግለሰቡ ግድያውን መፈፀሙን አምኖ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን በአዕምሮ ጤና ምክንያት ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ተከራክሮ በሎዴርዴል ካውንቲ እስር ቤት ውስጥ የፍርድ ሒደቱን እየተጠባበቀ ሳለ ነበር የጠፋው።

ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተነግሯል።