ወደ ሦስት ሚሊየን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ወደ ፖላንድ መሰደዳቸው ተገለጸ

ዩክሬናውያን ስደተኞች በምሥራቅ ፖላንድ ፕርዜምስል ባቡር ሲጠብቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ 2.9 ሚሊየን ዩክሬናውያን ስደተኞች ወደ ፖላንድ መግባታቸውን የፖላንድ የድንበር ጠባቂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ይኹን እንጂ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ድንበር አቋርጠው ወደ አገሪቷ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ እንደሆነና ወደ ዩክሬን የሚገቡት ግን ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱንም ኤጀንሲው ገልጿል።

ከፖላንድ ወደ ዩክሬን የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ከሚገቡት እንደሚበልጥም ኤጀንሲው አርብ ዕለት በትዊተር ገጹ አስታውቋል።

ከፖላንድ 23 ሺህ 800 ሰዎች ወደ ዩክሬን የገቡ ሲሆን 17 ሺህ 700 ሰዎች ደግሞ ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ገብተዋል ብሏል።

በአጠቃላይ ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ 825 ሺህ 800 ሰዎች ከፖላንድ ዩክሬን የገቡ ሲሆን የስደተኞች ቀውስ ከፍተኛ በሆነበት መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ 142 ሺህ 300 ሰዎች ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ተሰደዋል።

ከጦርነቱ በፊት፣ የዩክሬንን ድንበር አቋርጠው ወደ ፖላንድ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በአንድ ቀን በአማካይ 16 ሺህ 800 ነበር።

ይኹን እንጂ አሁን ላይ የተወሰኑ ስደተኞች ከፖላንድ ወጥተዋል። የዋርሳው ዩኒቨርሲቲ የስደተኞች ጥናት ፕሮፌሰር ማሴይ ዱዝዚክ በግምት ከ1.3 እስከ 1.4 ሚሊየን ያህል ሰዎች ፖላንድ እንደቀሩ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከልም 900 ሺህ ዩክሬናውያን የፖላንድ ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ የዩክሬንን ደቡባዊ ክፍል እንዲሁም ዶንባስ ክልልን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዓላማ እንዳላት የሩሲያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ተናግረዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሜጀር ጄነራል ሩስታም ሚኔካየቭን ጠቅሶ እንደዘገበው አካባቢዎቹን የመቆጣጠሩ ዓላማ ሞስኮ ወደ ክሬሚያ ለመግባት ድልድይ ለመስራት ያስችላል።

ከዚህም ባሻገር ሞስኮ በሩሲያ ወደሚደገፈውና ሞልዶቫ በሚገኘው ትራንስኒስትሪያ ተገንጣይ ክልል ለመግባት ዕድል ይሰጣታል ተብሏል።

ትራንስኒስትሪያ ከዩክሬን ምዕራባዊ ክፍል ጋር የምትዋሰን ትንሽ ክልል ናት።

የጄነራሉ አስተያየት በክሬምሊን በይፋ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው ግልጽ ባይሆንም በኢንተርፋክስ እና ታስ የዜና ኤጀንሲዎች ጨምሮ በሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በስፋት ተጠቅሰዋል።

የሩሲያ የመከላከያ ባለሥልጣናት የጄነራሉን አስተያየት "እየተመለከቱት" እንደሆነ ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን ይህ ከተረጋገጠ ሩሲያ በሚቀጥሉት ሳምንታት ስለያዘቻቸው ዕቅዶች የመጀመሪያ ግንዛቤ ይሰጣል።