የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆሙ ተገለጸ

ፊንጫኣ

የፎቶው ባለመብት, Eth Sugar Corp

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ በአካባቢው ካለ የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የስኳር ምርት ሥራውን ማቋረጡን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የስኳር ኮርፖሬሽን ቃል አቀባይ አቶ ረታ ደመቀ፤ በአካባቢው ባለው የደኅንነት እጦት ምክንያት ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን ነዳጅ ማቅረብ ባለመቻሉ ፋብሪካው ከአንድ ሳምንት በፊት ምርት ለማቆም መገደዱን ተናግረዋል።

"በአካባቢው ባለው የደኅንነት ችግር ምክንያት ወደ ፋብሪካው ነዳጅ ማቅረብ ባለመቻሉ ከየካቲት 02/2014 ዓ.ም ወዲህ እንደቆመ ነው ያለው" በማለት ተናግረዋል።

ብሉምበርግ የተሰኘው የዜና ምንጭ ፋብሪካው ሥራውን ለማቆም የተገደደው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠረው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን በፋብሪካው ላይ ባደረሰው ጥቃት ነው ሲል ዘግቦ ነበር።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የስኳር ኮርፖሬሽን ቃል አቀባይ እና ሌላ የፋብሪካው ሠራተኛ በፋብሪካው ላይ ጥቃት ተፈጽሞበታል መባሉን ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

"በአከባቢው የደኅንነት ችግር ስላለ እንጂ በፋብሪካው ላይ የተፈጸመ ጥቃት የለም" በማለት የንዳጅ አቅርቦት ችግር የፋብሪካውን ሥራ እንዳስተጓጎለው ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ተክል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia Sugar Corporation

የምስሉ መግለጫ, የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ተክል

አቶ ረታ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ካደረጉ በኋላ መልሰው እንዳስታወቁት፤ ነዳጅ ፋብሪካው ጋር በመድረሱ ፋብሪካው ወደ ሥራ እንደሚመለስ ገልጸዋል።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ ፋብሪካው ሥራውን አቋርጦ የነበረው በነዳጅ እጥረት እንጂ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት እንዳልሆነ ተናግሯል።

"ነዳጅ አጥቶ ቆሞ ነበር። ዛሬ ደግሞ ሥራ ጀምሯል" በማለት ይህ ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የፋብሪካ ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ለቀናት ሥራ ማቆሙ በስኳር አቅርቦት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ምን ያክል ነው ተብለው የተጠየቁት አቶ ረታ ደመቀ፤ "የስኳር ኢንዱስትሪ ለቀናትም ቢሆን ሥራ ማቆም የለበትም። 24 ሰዓት የሚሰራ ፋብሪካ ለ4 እና 5 ቀናት ሥራ ማቆሙ ችግር ነው። ጉዳቱ ይህን ያህል ነው ማለት ግን አይቻልም" ብለዋል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ግዙፉ ስኳር አምራች ፋብሪካ ነው በሚባለው ተቋም ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ እንደነበር አቶ ረታ ይናገራሉ።

"የተወሰኑ ትራክተሮች ተቃጥለው ነበር። ማን ነው ያቃጠለው የሚለውን የደኅንነት ሰዎች ናቸው መለስ መስጠት የሚችሉት። እንዲህ አይነት ችግር አጋጥሞ ነበር። . . . አራት ትራክተሮች በመቃጠላቸው ሥራ አልቆመም ነበር። አሁን ሥራ ለመቆሙ ምክንያቱ የነዳጅ እጥረት ነው" ብለዋል::

ይህ ፋብሪካው ከደኅንነት ችግር ጋር በተያያዘ ሥራ ለማቆም ስለመገደዱ የተሰማው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የታጣቂ ቡድኑን እንቅስቃሴ ተከትሎ የዜጎች ግድያ እና መፈናቀል በስፋት እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው።

ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ በፊንጫ ሸለቆ ውስጥ ልዩ ስሙ አገምሳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ይገኛል።

ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ፋብሪካው በዓመት 270ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም አለው። ፋብሪካው ከስኳር ምርቱ በተጨማሪ ኢታኖል በማምረት ከቤንዚል ጋር ተደባልቆ ለተሸከርካሪዎች በነዳጅነት እንዲውል ያደርጋል።