የትግራይ እስልምና አመራሮች ከኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን አስታወቁ

አል ነጃሺ መስጂድ
የምስሉ መግለጫ, አል ነጃሺ መስጂድ

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጡን የካቲት 05/2014 ዓ.ም ይፋ አደረገ።

የትግራይ እስልምና አመራሮች ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት በጥቅምት ወር መጨረሻ ለተነሳው ጦርነት ምክር ቤቱ ድጋፍ ሰጥቷል እንዲሁም በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ ባለማውገዙ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሃጂ መሐመድ ካሕሳይን ዋቢ አድርጎ ድምፂ ወያኔ እንዳሰፈረው በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች በጦርነቱ ተገድለዋል።

"ይህ ሁሉ ግፍ በትግራይ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ወንጀሉን ከማውገዝ ይልቅ ተባባሪ መሆኑ የሚኮነን ተግባር ነው" ብሏል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን "የዘር ማጥፋት ከመኮነን፣ ከማሸማገል ይልቅ ጦርነቱን ባርከው አስጀምረዋል" ያለው መግለጫው እንዲሁም ለጦርነቱ በገንዘብ፣ በመንፈስም ድጋፍ ማድረጋቸውን አትቷል።

"ይህ ተግባርም ከእስልምና ሕግና ሥርዓት ያፈነገጠ በመሆኑ ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጧል" ብሏል።

በጥንታዊው አል ነጃሺ መስጊድ ላይ የደረሰውን ጥቃት መግለጫው የጠቀሰ ሲሆን በጦርነቱ መጀመሪያ ወራት ወቅት መስጊዱ በጦር መሳሪያ ጉዳት ደርሶበታል።

የትግራይ ነዋሪዎች የመንግሥት ኃይሎችና የኤርትራ ሠራዊት መስጊዱን አውድመዋል ሲሉ ይከሳሉ። ይህ ጥንታዊ መስጊድ በነብዩ መሐመድ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በተሰደዱ የመጀመሪያ ሙስሊሞች የተሰራ ስለመሆኑ ይታመናል።

ከሰሞኑ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመውጣት የራሷን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለመመስረት መወሰኗን የትግራይ ሃይማኖት አባቶች አስታውቀዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤትን አስተያየት ለማግኘት ቢቢሲ የሞከረ ሲሆን፣ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ሦስት ሰዎችን አናግሮ ዜናውን የተመለከቱት ትናንት ምሽት እንደሆነና በጉዳዩም ላይ በመምከር ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የትግራይ ካህናት ከኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተለይተው የተናጠል ሲኖዶስ እንደሚመሰርቱ ያስታወቁ ሲሆን አስካሁን ቤተክርስቲያኗ በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር የለም።

ከኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ጥንታዊ፣ ከፍተኛ ተከታዮች ያሏት እና በአገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ተጽእኖ አላት።

ተንታኞች እንደሚሉት 40 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ባለባትና 34 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሙስሊሞች በሆኑባት ኢትዮጵያ የእምነት ተቋማቱ ክፍፍል ጉልህ ምዕራፍ እንደሆነ ይነገራል።

በዚህም ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ መከፋፈሉን ማሳየቱን ተጠቅሷል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ተቋማት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና የትግራይ መሪዎችን አነጋግረዋል።

ከሰሞኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል ንግግሮች መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ የትግራይና አማራ ክልሎችን ከጎበኙ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ" በማለት አስረድተዋል።

ከሳቸው በተጨማሪም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መግለጻቸው ይታወሳል።