በኢትዮጵያ፣ በዩክሬን እና በሌሎችም አገራት የቱርክ ድሮኖች የጦርነት ቅርጽን እንዴት ቀየሩ?

ቱርክ ሠራሹ ባይራክታር ቲቢ2

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቱርክ ሠራሹ ባይራክታር ቲቢ2

በመላው ዓለም ያሉ ወታደራዊ ግጭቶች በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አማካይነት አካሄዳቸውን እየለወጡ ነው።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንስቶ የተለያዩ አገራት ግጭቶች በሰው አልባ አውሮፕላን ምክንያት የኃይል ሚዛን ለውጥ ታይቶባቸዋል።

ከሰሞኑ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በተከሰተው ውጥረትም የድሮን ሚና ቀላል አይደለም።

ከእነዚህ ሁለት አገራት በስተ ደቡብ የምትገኘው ቱርክ በሰው አልባ አውሮፕላን ምርት ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳል።

ዩክሬን ራሷን ከሩስያ የምትከላከለው በቱርክ ሠራሽ ድሮኖች ሊሆን ይችላል።

በእርግጥ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ከሞላ ጎደል የቱርክ ድሮኖችን ማግኘት እየተለመደ መጥቷል።

ቱርክ በድሮን ምርት ምን ያህል ገናና ናት?

ቱርክ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል ናት። በምዕራባውያኑ ወታደራዊ ስብስብ ኔቶ ውስጥ ያለች ብቸኛው ሙስሊም አገር ናት ቱርክ።

በቱርክ የሚኖሩት ገለልተኛ ወታደራዊ ተንታኝ አርዳ ሜቭሉቶግሉ "የአንካራው መንግሥት ላለፉት 20 ዓመታት አስተማማኝ የድሮን ኃይል አዘጋጅቷል" ይላሉ።

ቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖቿን የአገር ውስጥ ደኅንነት ለማስጠበቅና ከድንበሯ በዘለለም ጥቅም ላይ እንዳዋለችው ይናገራሉ።

እአአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ የኩርድ ተገንጣይ ታጣቂዎች ላይ የደረሰው ጥቃት በዋነኛነት ይጠቀሳል።

የቱርክ መከላከያ አቅም ግንባታ ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው ለድሮን እንደሆነ ተንታኙ ያስረዳሉ።

"በምርት ጥራትና ብዛት ድሮን ቅድሚያ ይሰጠዋል። ቱርክ በቀጠናው በአስተማማኝ አቋም በመገንባት ከእስራኤል ውጭ የሚበልጣት" ይላሉ

ቱርክ ውስጥ ሰው አልባ በራሪ መሣሪያዎች ወይም በእንግሊዘኛው unmanned aerial vehicles (UAVs) የሚያመርቱ ሁለት ግዙፍ ፋብሪካዎች አሉ።

ባይካር መከላከያ የተባለው ፋብሪካ ባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) እና ባይራክታር አኪንቺ (Bayraktar Akinci) ድሮኖች ያመርታል።

ባይራክታር ቲቢ2 በሙከራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባይራክታር ቲቢ2 በሙከራ ላይ

የፋብሪካው ዋና የቴክኒክ ኃላፊ ሴልሁክ ባይራክታር የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ልጅ ባል ነው።

ሌላው ግዙፍ ድሮን አምራች ተርኪሽ ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪስ ሲሆን፤ ታይ አንካ (TAI Anka) እና ታይ አኩሱንገር (TAI Aksungur) የተባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ያመርታል።

የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ አርዳ ሜቭሉቶግሉ እንደሚሉት፤ የቱርክ መከላከያ እና ደኅንነት ተቋሞች ከእነዚህ ድሮኖች 150 የሚሆኑትን ያበራሉ።

ይህም ከአነስተኛ የስለላ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ካሚካዚ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጨማሪ ነው።

ቱርክ እና ዩክሬንን ምን አገናኛቸው?

እአአ በ2019 ቱርክ ለዩክሬን ብዙ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች ሸጣላታለች።

ዩክሬን ከቱርክ ጎን ኔቶን መቀላቀል ትፈልጋለች።

ዩክሬን ሩሲያ ከምትደግፋቸውና በምሥራቃዊ ክፍል ከሚንቀሳቀሱ አማጺያን ጋር ትግል ገጥማለች።

ከሩሲያ ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትም ያሰጋታል።

ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ወታደሮቿን በተጠንቀቅ አሰልፋ ትገኛለች።

ያለፈው የካቲት ኤርዶዋን ወደ ዩክሬን አቅንተው በሁለቱ አገራት መካከል ተጨማሪ የድሮን ግብይት የሚፈቅድ ስምምነት ፈርመዋል።

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስተር ስምምነቱ የቱርክ ድሮን አምራቾች ዩክሬን ውስጥ እንዲሠሩ መንገድ የሚከፍት እንደሆነ ለሮይተርስ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ያሳለፍነው ጥቅምት ዩክሬን የቱርክን ድሮን ተጠቅማ ሩሲያ የምትደግፋቸው ተገንጣዮች ይገለገሉበት የነበረ ዲ30 የአየር መሣሪያን ማውደሟን አስታውቋለች።

ሩሲያ ይህንን ተከትሎ ቱርክ የምትሸጣቸው ድሮኖች ቀጠናውን "ሰላም እየነሱ" እንደሆነ ኮንናለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ቱርክ ሩሲያ እና ዩክሬንን ላሸማግላችሁ ብላለች። ሽምግልናው ከድሮን ሽያጭ ጋር መጋጨቱ ግን አይቀርም።

የሶርያ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የቱርክ እና የሩሲያ ግንኙነት ውጥረት የነገሠበት ነው።

ሁለቱ አገሮች ሶርያ ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ቢኖራቸውም ለመስማማትም ፍላጎት አሳይተዋል።

ቱርክ ኤስ400 (S-400) የተባለ የአየር መከላከያ ከሩሲያ መግዛቷ የወዳጅነት መጀመሪያ ተደርጎ ተወስዷል። የመሣሪያ ግዢውን ኔቶ እና አሜሪካ ተችተውታል።

ዩክሬን ስንት ባይራክታር ቲቢ2 እንዳላት በውል አይታወቅም።

ነገር ግን ድሮኖቹ በዶንባስ ቀጠና ያሉትን አማጽያን ለመዋጋት እንደሚረዳት ይታመናል።

እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ዘመነኛ ካሜራ፣ ከተቆጣጣሪ ሥርዓት ጋር የሚያስተሳስር መሣሪያ እንዲሁም ኢላማ አስተካካይ ቁልፍ ተገጥሞላቸዋል።

ይህም ኢላማን አስተካክሎ ፈንጂ ለመጣል ያስችላቸዋል።

ወታደራዊ ተንታኙ አርዳ ሜቭሉቶግሉ እንደሚሉት፤ እነዚህ ድሮኖች ተንቀሳቃሽ ቡድንን ኢላማ ለማድረግ ይመረጣሉ።

"ሆኖም የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል በብዛትም በቴክኖሎጂ ረቂቅነትም ከዩክሬን ይልቃል" ይላሉ።

የቱርክን ድሮኖች የሚጠቀሙት የትኞቹ አገራት ናቸው?

ቱርክ ሠራሽ ድሮኖች የሚገዙ አገራት ቁጥር እየናረ መጥቷል።

የአገሪቱ የኤክስፖርት ዝርዝር ምን ያህል ድሮን እንደሚሸጥ አይጠቁምም።

ነገር ግን ከ15 አገራት በላይ ቱርክ ሠራሾቹን ባይራክታር እና ታይ ድሮኖች እንዳዘዙ ይታወቃል።

ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች በሶሪያ፣ ሊቢያ እና በናጎርኖ-ካራባግህ (በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል ለ44 ቀናት ውጊያ የተካሄደበት) ጦርነቶች ውጤታማ ከሆኑ በኋላ ፈላጊያቸው ተበራክቷል።

በዚህ ጦርነት የአዚሪ ኃይሎች የአርሜኒያን ወታደሮች፣ የውጊያ ተሽከርካሪዎች እና የአየር ኃይል የመቱት በቱርክ ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ነው።

ይህም አወዛጋቢው ግዛት በእጃቸው እንዲገባ አግዟቸዋል።

አምና የፖላንድ መከላከያ ሚኒስትር ከቱርክ 24 ተዋጊ ድሮኖች እንደሚገዙ አስታውቀዋል። ግዢው ፖላንድን ከኔቶ አባል አገራት የመጀመሪያዋ ያደርጋታል።

ለቱርክ አፍሪካም ትልቅ ገበያዋ ናት።

በቱርክ የሚኖሩት ገለልተኛ ወታደራዊ ተንታኝ አርዳ ሜቭሉቶግሉ "በአፍሪካ ገበያ የቻይና አምራቾች ዋነኛ ተቀናቃኝ ቱርክ ነች። የቱርክ ርካሽ ድሮኖች የኔቶን የጥራት ልኬት የጠበቁም ናቸው" ይላሉ።

የቱርክን ድሮኖች ከገዙ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ ሩዋንዳ እና ናይጄርያም ይጠቀሳሉ።

ቱርክ እና ኢትዮጵያ ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ሆኖም ስለ ድሮን ግብይት በግልጽ ይፋ አልተደረገም።

አምና የቱርክ ኤክስፖርት ሪፖርት የበረራ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት እንዳሳየ ይጠቁማል።

ያሳለፍነው ጥቅምት ላይ አሜሪካ፤ ቱርክ ለኢትዮጵያ ድሮን እየሸጠች መሆኑ እንዳሳሰባት ተናግራለች።

ወጣም ወረደ ቱርክ ለምታመርታቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች አዲስ ገበያ ከማፈላለግ የምትቦዝን አይመስልም።

ወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ "የድሮን ሽያጭ ዘላቂነት ያለው ወታደራዊ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር ያስችላሉ። ይህም ቱርክ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና እንድትፈጥር ያግዛታል" ይላሉ።

አፍሪካ ውስጥ ያለውን የገበያ ፍላጎት ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ጠንቅቀው ተገንዝበዋል።

ጥቅምት ላይ "አፍሪካ ውስጥ የትም አገር ስሄድ የምጠየቀው ስለ ሰው አልባ አውሮፕላን ነው" ብለው መናገራቸው ይታወሳል።