ከሩሲያ ጋር የተፋጠጠችው ዩክሬን ተራ ዜጎቿ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወሰዱ እያደረገች ነው

የዩክሬን ዜጎች በወታደራዊ ስልጠና ላይ
የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን ዜጎች በወታደራዊ ስልጠና ላይ

ዲሚትሮ ዱባስ ጦርነትን ዳግም አያለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም። እሱ የተሳተፈበት ጦርነት እንዳከተመለት ነበር የሚያምነው።

ሆኖም ግን አሜሪካ፤ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር እንደምትችል ደጋግማ እያስጠነቀቀች ነው። አገሩ ላይ የተቃጣ ነው የሚባለውን ይህንን ሁኔታ በጎ ፈቃደኛ ተዋጊ ዲሚትሮ ዱባስ ችላ ሊለው የሚችለው ጉዳይ አልሆነም። እጅግ አስጨንቆታል።

"እንዲውም ባለፈው ሳምንት በጣም ተረብሼ ነበር። እርዳታ ለማግኘት ወደ ሥነ ልቦና ባለሙያ ጋር ሁሉ ሄጄ ነበር" ሲል ተናግሯል።

ለወራት የዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮች ድንበር አቅራቢያ የሩሲያ ወታደሮች እንደሰፈሩ እየጠቆሙ ነው። እነዚህ ጥቆማዎችና ማስጠንቀቂያዎች የቭላድሚር ፑቲን ወታደሮች እንዴት ወደ ዩክሬኗን ዋና ከተማ ኪዩቭ እንደሚገሰገሱ ሁሉ የሚናገሩ ናቸው።

የወረራው ቀጥተኛ ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉት ዩክሬናውያን ይህ ስለ መሆኑ እርግጠኞች አይደሉም። ሆኖም የሚሰሙት ወሬዎች ሁሉ ተስፋ የሚሰጡ አይደሉም።

በኪዬቭ የሚኖረው ዲሚትሮ "ሩሲያ በየትኛውም ጊዜ በቀናት ውስጥ ወታደሮቿን ወደ ድንበሩ ማንቀሳቀስ እና መውረር ትችላለች። ስለዚህ ይህ ዝግጅት ምንም የተለየ አይደለም" ሲል ይገልጻል።

ዲሚትሮ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የሽያጭ ሠራተኛ ነበር። በዚያው ዓመት በሩሲያ ከሚደገፉ ኃይሎች ጋር ከባድ ውጊያ ተቀሰቀሰ። እሱም ይህንን ውጊያ ከበጎ ፈቃደኛ ወታደሮች ጋር በመሆን ተቀላቀለ።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከነበረው ዓመት ጀምሮ የተኩስ አቁም ተፈርሟል። ነገር ግን ይህ ስምምነት ተግባራዊ የመሆኑ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ማንኛውም ችግር በማንኛውም ጊዜ ሊቀሰቀስ ይችላል።

ሆኖም ጦርነቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ዲሚትሮ ወደ መደበኛ ሥራና ህይወት ተመልሶ ነበር።

ለአስከፊው ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን ራሱ አሳምኖ ተረጋግቷል። መኪናውን በነዳጅ ሞልቷል። ለችግር ጊዜ የሚሆነውን ምግብም የገዛ ሲሆን የበጎ ፍቃደኛ ተወጊ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ምናልባት የረሳውን የመሳሪያ አጠቃቀም እና የጦርነት ልምድን ዳግም እንዲያስታውስ ይረዳው ይሆናል።

የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች ኪዬቭን መክበብን ጨምሮ ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በተመለከተ ያላቸውን ሁሉንም ዓይነት እቅዶች ይፋ አድርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ ዲሚትሮን ጨምሮ በርካታ መደበኛ ዜጎች የጦር ልምምድ እያደረጉ ባለበት ጊዜ ትምህርት ቤቶችም ቦምብን እና የአየር ጥቃቶችን የመከላከል ስልጠናዎችን እየሰጡ ነው። ይህ ስልጠና ጥቃት በሚከፈት ጊዜ ደኅንነትን ጠብቆ እንዴት ማምለጥንም ያካትታል።

በወታደራዊ ስልጠናው ጡረተኞችን ጨምር ቅዳሜና እሁድ ልምምዶችን እያደረጉነው። ከኪዬቭ አቅራቢያ ባለ ጫካ ውስጥ ፋብሪካ ፍርስራሾች በጦር ሜዳ መልክ በተዘጋጀ ቦታ ላይ ልምምድ ይደርጋ። ስልጠናውን ለመውሰድ እድሜያቸው የገፉ ሰዎች እየተመዘገቡ ሲሆን አሰልጠኞቹም ያህንን እንዳያደርጉ አይከለሏቸውም።

የ61 ዓመቱ አዛውንት ቫሲል ናዛሮቭ በበረዶ ላይ በደረታቸው ተኛተው መሳሪያቸውን አቀባብለው ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ ምናባዊ ጠላት ላይ ተኩስ ይከፍታሉ። ሆኖም አሁን ላይ ሩሲያውያን ዩክሬንን ይወርራሉ ብለው አያስቡም።

ቫሲል ናዛሮቭ ከእንጨት የተሰራ የመለማመጃ ጠመንጃ ይዘው
የምስሉ መግለጫ, ቫሲል ናዛሮቭ ከእንጨት የተሰራ የመለማመጃ ጠመንጃ ይዘው

የጦር ልምምድ ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው ነው። ታዲያ በመጀመሪያው የልምምድ የታጠቁት "መሳሪያ" በእንጨት የተቀረጸ እንጂ እውነተኛ አይደለም።

"ኪዬቭ ይመጣሉ ብዬ አላምንም ግን ይሆናል ብለን መዘጋጀት አለብን" ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላኛው በልምምድ ላይ ያሉት የ64 ዓመቱ አዛውንት ሰርሂ ካሊኒን አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎታቸውን ካጠናቀቁ ቆይተዋል። ሆኖም ሰሞነኛ ሁኔታውን ተከትሎ ዳግም ወደ ስልጠና ገብተዋል "የምዕራቡ ዓለም ኃይለኛ የማዕቀብ ዛቻ ፑቲንን የሚያቆመው ይመስለኛል" ሲሉ አስተያየታቸውን የገለጹ ሲሆን "ጠላት ድንበራችን ጋር ነው ስለዚህ ሁሉም ዝግጁ መሆን አለበት" በማለት አክለዋል።

በግል ይዞታ ስር በሚገኘው እና ፕራይምዪ የሚል ስያሜ ባለው የዩክሬን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሩሲያ ወደ 100,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ድንበር ማሰማራቷ ቁጥር አንድ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

በቴሌቪዥን ጣቢያው በአቅራቢነት የሚሰራው ታራስ ቤሬዞቬትስ የሩሲያን ፕሬዝዳንት "ተገማች" አይደሉ በማለት የገለጻቸው ሲሆን፣ ዩክሬን ሉዓላዊ አገር ሆና አታውቅም ብለው ያስባሉ ሲሉ ገልጾቸዋል።

ጋዜጠኛው "ፑቲን የሶቪየት መሪዎች ለአስርት ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ እንዳደረጉት ሁሉ ዩክሬን በምርጫዋ መንቀሳቀስ እንድታቆም ይፈልጋል" ብሏል።

ጋዜጠኛው መሰረቱ ሩሲያ ነው መሰረቴ የሞስኮ ደጋፊ ወይም የማንኛውም "የሩሲያ ዓለም" አካል ደጋፊ አያደርገኝም ሲል ገልጿል።

"በአውሮፓውያኑ 2014 ምርጫችንን አድርገናል። ምርጫው ግልጽ ነው። የሩሲያ ግዛት አካል መሆን አንፈልግም" ሲል በአጽኦት ተንግሯል።

"ወደ አውሮፓ ሕብረት ወይም ናቶ የመቀላቀል ዕድል ባይኖረን እንኳን ግባችን የምዕራባውያኑ ስልጣኔ አካል መሆን ነው። ይህም ማለት የሕግ የበላይነት፣ የመናገር ነፃነት ያለበት አገር ማለት ነው። እነዚህ ዩክሬናውያን ልፋለሙላቸው የቆረጧቸው ነገሮች ናቸው" ሲሉም ተደምጧል።

የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች ከሚያቀርቡት መረጃ በተቃራኒ ዲሚትሮ ዱባስ እና ጓደኞቹ በዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚደረገው ፍልሚያ በቅርቡ እንደሚሆን አያምኑም።

ዲሚትሮ "የዩክሬን ትልቁ ራስ ምታት ከሩሲያ አጠገብ መሆኗ ነው" በሚል አባባሉ ይታወቃል።

አገሪቱ ከዚህ ቀደም በበርካታ ቀውስና ውጣ ውረዶች ማለፏን የሚገልጸው ጋዜጠኛው ከ1986 የቼርኖቤል የኑክሌር አደጋ እንዲሁም ከተለያዩ ጦርነቶች አገግማ እስካሁን አለች ብሏል።

"ለዩክሬን ሁልጊዜ በእሳት ነበልባል ውስጥ መኖሩ የተለመደ ነው። በየቀኑ በየሰዓቱ ጦርነትን ማሰብ ያሳብዳል" ሲልም አክሏል።

"የሆነው ሆኖ ሩሲያን ብድግ አድረገን የሆነ ቦታ መውሰድ አንችልም። ጎረቤታችን ናት። ከእሷ ጋር መኖር አለብንም" ብሏል።