በዩኬ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ከ150 ሺህ በላይ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሞቱ ሰዎች ከ150 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት መንግሥት በሚያወጣቸው ዕለታዊ አኃዞች ተጨማሪ 313 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ የሟቾችን ቁጥር 150 ሺህ 57 አድርሶታል።
ዩናይት ኪንግደም ከአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ህንድ፣ ሩሲያ፣ ሜክሲኮ እና ፔሩን በመከተል ሟቾች ከ150 ሺህ በላይ ያለፈባት ሰባተኛዋ ሃገር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት እያንዳንዱ ሞት " ለጓደኞቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመድ አጠቃላይ ለማህበረሰቡ ከባድ ኪሳራ ነው። ሃሳቤና እና ሃዘኔም ከተጎጅዎች ጋር ነው ብለዋል"
ቦሪስ ጆንሰን አክለውም ኮሮናቫይረስ "በአገራችን ላይ አስከፊ ጉዳት አድርሷል" እና "ከዚህ ወረርሽኝ ነፃ የምንሆንበት መንገድ ያልተከተባችሁ በሙሉ ስትከተቡ ነው" ብለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም 146 ሺህ 390 የሚሆኑ አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም በከፍተኛ መጠን ከሚተላላፈው የኦሚክሮን ልውጥ ጋር በተያያዘ እንዳገረሸም ተነግሯል።
በባለፉት 28 ቀናት የሟቾች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን በባለፉት ሰባት ቀናትም የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 271 የደረሰ ሲሆን ይህም ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃጸር 38.3 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።
ሆኖም ኮቪድ-19 ሲጀምር እንደነበረው ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍልና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደቀደመው አለመሆኑ ከክትባቱ ተፅእኖ ጋር የተያያዘም ነው።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደ ሆስፒታሎች የሚገቡ ታማሚዎች ቁጥር እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ታመው በተደጋጋሚ መቅረት በጤና ማዕከላት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ተብሏል።
በስኮትላንድ በኮቪድ-19 ተይዘው ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ከ50 በመቶ በላይ ጭማሬ አሳይቷል።












