በኮቪድ ምክንያት በረራዎች በመሰረዛቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ለእንግልት ተዳረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽ መስፋፋት ባስከተለው የሠራተኞች እጥረት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ከጉዟቸው ተስተጓጉለዋል።
ካለፈው አርብ እና በፈረንጆቹ የገና ሰሞን ቅዳሜና እሁድ ከ7,500 በላይ በረራዎች መሰረዛቸውን 'ፍላይት አዌር' የተሰኘ የአየር መንገድ መረጃ መከታተያ ድረ-ገጽ አሳውቋል።
በእነዚህ በረራዎች መሰረዝ ወይም ለተጨማሪ ጊዜ መዘግየት የቻይና እና የአሜሪካ አየር መንገዶች በቀዳሚነት ከተጎዱት መካከል ናቸው።
የአየር ትራንስፖርት ኩባንያዎች በረራዎችን ለመሰረዛቸው ምክንያት የሆነው ሠራተኞቻቸው በኮሮናቫይረስ እየተያዙ በመሆናቸው ነው።
ቫይረሱ ያልተገኘባቸው እና በቫይረሱ ከተያዙት ጋር ንክኪ የነበራቸው ሠራተኞችም እራሳቸውን እንዲያገሉ እየተደረጉ ነው።
በዓለም ዙሪያ እየተመዘገቡ ያሉ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ሲሆን፣ ለዚህም በአብዛኛው አዲሱ የኦሚክሮን ቫይረስ ዝርያ በፍጥነት የመስፋፋት ያስከተለው ነው።
ምንም እንኳን ቀደም ተብለው የተደረጉ ጥናቶች ኦሚክሮን ከሌሎች የኮሮናቫይረስ ዓይነቶች የበለጠ ጉዳት እንደሌለው ቢያመላክቱም እየተመዘገበ ያለው ቁጥር ብዛት ግን ሳይንቲስቶችን እያሳሰበ ነው።
ትላንት ዕሁድ ከ2,400 በላይ በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን ከ800 በላይ የሚሆኑት ወደ አሜሪካ ወይም ወደ አሜሪካ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚሄዱ ወይም ከዚያ የሚነሱ እንደነበሩ የፍላይት አዌር መረጃ ያሳያል።
በዚህ ክስተት ክፉኛ የተጎዱት ዴልታ፣ ዩናይትድ እና ጄትብሉ የተሰኙ የአሜሪካ የአየር መንገድ የኩባንያዎች ናቸው።
ዩናይትድ ቀደም ብሎ ባወጣው ማስጠነቀቂያ የኦሚክሮን ዝርያ "በበረራ ሠራተኞቻችን እና ሥራችንን በሚመሩ ሰዎች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው" ያለ ሲሆን፣ የተስተጓጎሉ መንገደኞቹን ወደ ኤርፖርት ከመምጣታቸው በፊት እያነጋገረረ እንደነበረ ገልጿል።
አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ዋነኛው ስጋት ሆኗል።
በዚህ ዝርያ ምክንያት በጣም የተጎዳው አየር መንገድ ቻይና ኢስተርን ሳይሆን እንደማይቀር የሚገመት ሲሆን እሁድ ዕለት ብቻ ከ390 በላይ በረራዎች ተስተጓጉለዋል።
በቻይና ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ዢያን ከተማ ያለው ኤርፖርት ከ120 በላይ በረራዎች መሰረዙ ተዘግቧል።
ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ያዚያች ከተማ ነዋሪዎች ቤት እንዲቆዩ በአገሪቱ ባለሥልጣናት ታዝዘዋል። በሌላ በኩል በለንደን የሚገኘው ሄትሮው አውሮፕላን ማረፊያ እሁድ ዕለት ብቻ ከ60 በላይ በረራዎች ተሰርዘውበታል።
እንደ አሜሪካው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ አስካሁን በዓለም ዙሪያ ወደ 5.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ለህልፈት ተዳርገዋል። በቫይረሱ እንደተያዙ የተረጋገጡ ሰዎች ከ279 ሚሊዮን በላይ ሆኗል።















