ሳሙዔል ኤቶ የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሆኖ ተመረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ተጫዋች ሳሙዔል ኤቶ የካሜሮን እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ፌዴሬሽን የቀጣዩ አራት ዓመት ፕሬዝደንት ሆኖ ቅዳሜ ዕለት ተመርጧል።
አራት ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ኤቶ የካፍ አራተኛው ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ሰይዱ ንጆያን ረቶ ነው ሥልጣኑን የተቆናጠጠው።
ሰባት ዕጩዎች ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር ስማቸውን አስገብተው ደፋ ቀና እያሉ ቆይተው የምርጫው ዕለት አምስቱ ራሳቸውን አግልለዋል።
የ40 ዓመቱ ኤቶ የሃገሩን እግር ኳስ ለማሳደግ ብዙ ነገሮችን እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።
"እግር ኳሰኞችን ወደ ፖሊሲያችን ትኩረት ማምጣት አለብን" ሲል ከተመረጠ በኋላ ተናግሯል። "እኛ ኃላፊነታችን ይህንን ጨዋታ የሚጫወቱ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው" ሲልም አክሏል።
የቀድሞው የባርሴሎና፣ ኢንተር ሚላን እና ቼልሲ ኮከብ እሱ ሥልጣን ላይ እያለ ቢያንስ 10 ስታድየሞችን እንደሚገነባም ቃል ገብቷል።
"ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር አውርቻለሁ። መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ወደኋላ የማይሉና ሕልማችንን ሊያሳኩ የሚችሉ ሰዎች እንደምናገኝ አልጠራጠርም" ብሏል ኤቶ።
ኤቶ ለካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንትነት እንደሚወዳደር ሲያሳውቅ ብዙዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ተከታትለውት ነበር።
በሚቀጥለው ጥርና የካቲት ሃገሩ ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ስታስተናግድ ኤቶ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ ሆኖ ሁኔታዎችን ይከታተላል።
ቅዳሜ ዕለት ከነበረው ምርጫ ራሳቸውን ካገለሉ መካከል የቀድሞዎቹ ተጫዋቾች ማቦዋንግ ካሳክ እና ጁልስ ዴኒስ ኦናና ይገኙበታል።
የካሜሮን የምንም ጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ፤ አውሮፓ ካየቻቸው አፍሪካዊያን ኮከቦች መካከል አንዱ እየተባለ የሚሞካሸው ኤቶ በፈረንጆቹ 1996 የ16 ዓመት ታዳጊ እያለ ነው የስፔኑን ሪያል ማድሪድ የተቀላቀለው።
ከዚያም በውሰት ወደ ሌጋኔስ፣ ኤስፓንዮልና ማዮርካ አቅንቶ ተጫውቷል። ከማዮርካ ጋር የሚያዘልቀውን ውል የፈረመው ኤቶ በ2000 በ133 ጨዋታዎች 54 ጎሎችን ማስቆጠር ችሎ ነበር።
ከአራት ዓመታት በኋኃ ባርሴሎናን የተቀላቀለው ኤቶ ሶስት ጊዜ የላሊ ጋ ዋንጫን ሲያነሳ የካታላኑ ክለብ ሁለት ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል እንዲሆን አስችሏል።
በ2006 ኤቶ የስፓኒሽ ጎልደን ቡትን ያሸነፈ ከአህጉረ አፍሪካ የመጣ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆነ። በወቅቱ በ34 ጨዋታዎች 26 ጊዜ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችሎ ነበር።
ካሜሮናዊው አጥቂ ለባርሴሎና ባደረጋቸው 144 ጨዋታዎች 108 ጎሎች አስቆጥሯል። ከዚያ በኋላ ነው የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን ተቀላቅሎ ሶስተኛ የቻምፒየንስ ሊግ ድሉን ጨምሮ ሴሪ አ እንዲሁም የዓለም ክለቦች ዋንጫን ማንሳት የቻለው።
ከሃገሩ ካሜሮን ጋርም ሁሉት ጊዜ የአፍሪካን ትልቁን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። በኤቶ የተመራው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን በ2000 እንዲሁም በ2002 የአፍሪካ ዋንጫን አንስቷል።
አልፎም በ2000 ካሜሮን የኦሊምፒክ ሜዳሊያ እንድታገኝ ያደረገው ኤቶ በፍፃሜው ጨዋታ ጎል ማስቆጠሩ አይዘነጋም።












