በጀርመን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የተቀበረ ቦምብ ፈንድቶ ሰዎች አቆሰለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጀርመኗ ከተማ ሙኒክ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የተቀበረ ቦምብ የባቡር መስመር ግንባታ የሚደረግበት አካባቢ ፈንድቶ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል።
የከተማዋ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል እንዳለው ፍንዳታው ያጋጠመው 'ዶነርስበርገር' በሚባለው ድልድይ አካባቢ የቁፋሮ ስራ በመከናወን ላይ ሳለ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን ድልድዩ ደግሞ ከባቡር ጣቢያው በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው።
ፍንዳታውን ተከትሎም በሙኒክ የባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲገታ ሆኗል።
በዓለም ጦርነት ወቅት የተቀበሩና እስካሁን ያልፈነዱ ቦምቦች በጀርመን በተደጋጋሚ የሚገኙ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በከባድ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወገዱ ይደረጋል።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቦምቦች ምንም ጉዳት ሳያደርሱ በባለሙያዎች አማካይነት እንዲመክኑ ይደረጋሉ።
ፖሊስ በበኩሉ ፍንዳታው የተከሰተው በድልድዩ ስር የውስጥ ለውስጥ ቱቦ ለመቆፈር በሚሞከርበት እንደሆነ አስታውቋል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት ፍንዳታው ሲደርስ ከፍተኛ የሆነ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ወዲያውም አካባቢው በጭስ ታፍኗል።
ቁፋሮውን ሲያከናውን የነበረው ኤክስካቬተር በፍንዳታው ምክንያት ተገልብጦ ወድቋል። ነገር ግን በዚህ ምክንያት የሰዎች ሕይወት አላላፈም ተብሏል።
ፍንዳታው ከተሰማ በኋላም የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም ፈንጂ አምካኞች በቦታው ደርሰው ለሰዎች እርዳታ በማድረግና የቀረ ያልፈነዳ ቦምብ መኖር አለመኖሩን በመፈተሽ ተጠምደው ታይተዋል።
ደች ባህን የተሰኘው የባቡር አገልግሎት ሰጪ ከዋናው ማዕከል እና ወደ ዋናው ማዕከል የሚደረጉ የአጭር ሰአት ጉዞዎችን ሙሉ በሙሉ ያቋረጠ ሲሆን ፖሊስ ግን ረጅም ርቀት የሚጓዙ ባቡሮች ስራቸውን እንደጀመሩ አስታውቋል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዮአኪም ሀርማን ከአውሮፕላን የሚጣለው ፈንጂ 250 ኪሎግራም እንደሚመዝን አስታውቀዋል።
በጀርመን ከተሞች ያልፈነዱ ቦምቦች ሲኖሩ አልያም ይኖራሉ ተብሎ ሲገመት የአካባቢው ነዋሪ ለጊዜውም ቢሆን አካባቢውን እንዲለቅ ማድረግ የተለመደ ነገር ነው። ቦምቦቹ በዓለም ጦርነት ወቅት በብዛት በእንግሊዝና አሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች የተጣሉ ናቸው።
በሙኒክ ደግሞ ትልልቅ የግንባታ ስራዎች ሲከናወኑ የተቀበሩ ፈንጂዎች መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ምርመራና ጥንቃቄ ይደረጋል።
''እንዴት ይህ ቦምብ ቀድሞ እንዳልተገኘ አስቸኳይ ምርመራ ይደረጋል'' ብለዋል የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ።
በአውሮፓውያኑ 2017፣ 1.4 ቶን የሚመዝን የእንግሊዝ ቦምብ መገኘቱን ተከትሎ 70 ሺ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲሄዱ ተደርገው ነበር።








