እንግሊዝ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ዜጎቿ የመከላከያ ሃይሏ አባል እንዲሆኑ ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, Oliver Brown
እንግሊዝ በደማቸው ውስጥ የኤች አይቪ ቫይረስ የሚገኝ ብሎም ፕሮፍላክሲስ የተሰኘውን የጸረ ቫይረስ መድሃኒት የሚጠቀሙ ዜጎቿ የመከላከያ ሃይሏን እንዲቀላቀሉ መፍቀዷን ትላንት ተከብሮ በዋለው የአለም የኤድስ ቀን ላይ አስታወቀች።
እስከአሁን ድረስም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ሰዎች ሰራዊቱን ለመቀላቀል ማመልከት የማይፈቀድላቸው ሲሆን በሰራዊቱ ውስጥ እያሉ ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎችም መስራት የሚችሉበት ዘርፍ ላይ ገደብ ይደረግ ነበር።
ይህም «የሎጂስቲክስ ጫና» ያመጣል በሚል ምክንያት የተቀመጠ ገደብ ነበር።
«ለኤች አይቪ ኤድስ የሚሰጡ የመድሃኒት ህክምናዎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ሰዎች ህይወት ላይ አብዮት ሊባል የሚችል ለውጥ አምጥቷል» ያሉት የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ሊዮ ዶከቲ ናቸው።
«እንደ ስልጡን እና አካታች ቀጣሪ የሳይንስ ግኝቱን እውቅና መስጠታችን እና እርሱንም ለመተግበር ወደ ስራ መግባታችን ትክክለኛ ውሳኔ ነው» ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሮፍላክሲስ ወይም ፒአርኢፒ የተሰኘው መድሃኒት በቀን አንዴ የሚዋጥ እና ያለመከላከያ በሚደረግ ግንኙነት ወቅት ኤች አይቪ ቫይረስ እንዳይተላለፍ የሚያግዝ የጸረ ቫይረስ መድሃኒት ነው።
የመከላከያ ሚኒስቴሩም ለውጡ ይህንን መድሃኒት የሚጠቀሙ ሰዎችን የወሊድ መከላከያ እንደሚጠቀሙ ሰዎች እንደሚወስድም ይፋ አድርጓል።
ይህ ለውጥ ቀጥሎም በሚቀጥለው ዓመት በሰራዊቱ ውስጥ እያሉ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ ሰዎች የቫይረሱ መጠን በምርመራ የማይገኝበት ደረጃ ላይ ከደረሰ እንደማንኛውም አካላዊ ብቃት እንዳለው የሰራዊት አባል እንዲቆጠሩ ያርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዜናው እንደ ሌተና ኮማንደር ኦይል ብራውን ላሉ የሰራዊቱ አባላት ትልቅ ትርጉም አለው። ኮማንደሩ ከሁለት አመታት በፊት በሰራዊቱ ውስጥ በማገልገል ላይ ሳለ ነበር ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የተገኘው።
«ቫይረሱ እንዳለብኝ ሳውቅ መቼ ነው የምሞተው፣ ህይወቴ ምን ይመስል ይሆን እንዲሁም ስራዬን አጣ ይሆን የሚሉት ጥያቄዎች ነበር የመጡብኝ» ሲል ለራዲዮ ዋን ኒውስቢት ፕሮግራም ተናግሯል።
የ30 ዓመቱ ኦይል ቫይረሱ ከተገኘበት ጀምሮ «በሕክምና ምክንያት ለተልዕኮ ውሱንነት ያለበት» የሰራዊቱ አባል ተብሎ መቆየቱን እና በስራ ቦታው ባለው ሃላፊነትም ማሽከርከር ብሎም መርከቦችን የመዋጋት ስራ ላይ ብቻ ተገድቦ ቆይቷል።
«ውሱንነት ያለው ሰው ተብለህ መመደብህን እና በርግጥም ግን ምንም ውሱንነት እንደሌለህ ስታውቅ ለምን የሚል ጥያቄ እንድጠይቅ አድርጎኛል» ሲል ኦይል ተናግሯል።
በርግጥ ኦይል ወደ ሰራዊቱ ሳይቀላቀል ቫይረሱ በደሙ ቢኖር ኖሮ ቀድሞውንም ወታደር እንዲሆን አይፈቀድለትም ነበር።
«ይህ በሰራዊቱ ውስጥ ሌሎች ሰዎች በዚህ ጉዳይ ምክንያት እንደኔ አያዝኑም ብዬ አምናለሁ። ከዛ በላይ ግን ሌሎች በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ኤችአይቪ በደማቸው መገኘቱ እንደኔ ምቾች የማይነሳቸው ባልደረቦቼ አሁን ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱ ችግር እንዳልሆነ ይረዳሉ» ሲልም ኦይል ተናግሯል።












