የአሜሪካ ከፍተኛ ዳኞች የፅንስ ማቋረጥ ገደቦችን እንደሚደግፉ ጠቆሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ15 ሳምንታት እርግዝና በኋላ ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክለውን የሚሲሲፒን ግዛት ህግ ለመቀበል ያዘነበለ ይመስላል።
ይህም የፅንስ ማቋረጥ በመደፈርም ሆነ በዘመዶች መካከል እርግዝና ቢፈጠር ፅንሱ ከ15 ሳምንታት በላይ ከሆነ የሚከለክል ነው።
ይህንን አስመልክቶ ረቡዕ ዕለት በዋለው ችሎት ወግ አጥባቂ ዳኞች በርካቶች የህጉ መፅደቅን እንደሚደግፉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰኔ ወር ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የፅንስ ማቋረጥ እድላቸውን ሊያሳጣ እንደሚችልም ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
ፅንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ተሟጋቾች ፍርድ ቤቱን "ያልተወለዱ ህፃናትን እንዲጠብቅ እያሳሰቡ ነው"።
ነገር ግን ፅንስ ማቋረጥ ከተገደበ የእናቶች ሞት ቁጥር እንደሚያሻቅብ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
የፅንስ ማቋረጥ ጉዳይ በአሜሪካ በርካቶችን የሚያወዛግብ ሲሆን የክርክሩ ሁለቱም ወገኖች ፅንፍ ላይ ያሉና አስማሚ ነጥብ ላይ ሊደርሱም አልቻሉም።
የሚሲሲፒን ህግ የሚደግፉ ጠበቆች ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የተላለፉ ሁለት ውሳኔዎችን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲሽር ጠይቀዋል።
የመጀመሪያው በአውሮፓውያኑ 1973 የፀደቀውና 'ሮ ቨርሰስ ዌድ' የሚል ስያሜ ያገኘው ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት እርግዝና ወቅት የማስወረድ ፍፁም መብት እና ከዚያ በኋላ ባሉት ወራቶች ደግሞ የተገደበ መብት የሰጠ ውሳኔ ነው።
ሌላኛው በአውሮፓውያኑ 1992 የፀደቀው 'ፕላንድ ፓረንት ሁድ ቨርሰስ ኬሲ' ተብሎ የሚታወቀው ነው።
በዚህም ውሳኔ መሰረት ፅንስ ከማህፀን ውጭ መቆየት ከሚችልበት ጊዜ በፊት ወይም በ24 ሳምንት ውስጥ ያሉ ፅንሶችን ማቋረጥ በሚፈልጉ ሴቶች ላይ "ያልተገባ ሸክም" ግዛቶች ሊጭኑ አይችሉም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፅንሱ ከማህፀን ውጭ መኖር የሚችለውን የጊዜ መስፈርት በመውሰድ በፅንስ ማቋረጥ ውስጥ ዋነኛ ሁኔታ ሆኖ አገልግሏል።
ይህም ማለት ከዚህ ጊዜ በፊት የፅንስ ማቋረጥ ላይ ያለ ማንኛውንም እገዳ ይከለክላል።
ነገር ግን የፀረ ፅንስ ማቋረጥ ዘመቻ አራማጆች በፍርድ ቤቱ የተሾሙት ዳኞች ርዕዮተ ዓለም አዲስ እድል እንደፈጠረ ተስፋ ያደርጋሉ።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሾሙት ሶስት ዳኞች በፍርድ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ በመፍጠር በዘመናዊቷ የአሜሪካ ታሪክ ወደ ወግ አጥባቂነቱ ያዘነበለ ፍርድ ቤት መመስረት ችለዋል ተብሏል።












