ጦርነቱን በመሸሽ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎች ከሸኖ እንዳያልፉ መደረጉ ተነገረ

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በመሸሽ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሞከሩ ሰዎች ኦሮሚያ ክልል ከምትገኘው የሸኖ ከተማ እንዳያልፉ እየተደረገ መሆኑን ተፈናቃዮች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ከደቡብ ወሎ ከተሞች ተፈናቅለው አዲስ አበባ ለመግባት ጥረት ያደረጉ ተፈናቃዮች፤ የነዋሪነት መታወቂያቸው ሸኖ ከተማ ላይ ታይቶ ወደ መጡበት እንዲመለሱ እንደተደረጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቂምቢቢ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ነጋሽ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በርካታ ሲቪሎች እና የመከላከያ አባላት ከጦርነቱ ቦታዎች በመውጣት በወረዳዋ በኩል አድርገው ለማለፍ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በርካቶች እየተለዩ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ ኃይሉ አዱኛ በተመሳሳይ ተፈናቃዮች ከሸኖ ከተማ እንዳያልፉ እና ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መደረጋቸውን አረጋግጠዋል።

ቂምቢቢ ወረዳ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ስትሆን ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጋር ትዋሰናለች።

ሸኖ ከተማ ደግሞ የቂምቢቢ ወረዳ ዋና ከተማ ናት።

ሸኖ ከተማ ጦርነቱን በመሸሽ አዲስ አበባ መግባት ለሚሹ ሰዎች መተላለፊያ አማራጭ ሆኖ ቆይታለች።

'ማለፍ የሚችለው የአዲስ አበባ መታወቂያ ያለው ነው'

ለደህንነት ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ የነበረ ተፈናቃይ፤ ባለፈው ቅዳሜ ከኮምቦልቻ ከተማ ወጥቶ የትራፊክ መጨናነቅ ስለነበረ ሸኖ የደረሰው እሁድ ጠዋት መሆኑን ያስታውሳል።

"ሸኖ አካባቢ የነበሩ ትራፊክ ፖሊሶች፣ ፖሊሶች እና ልዩ ኃይሎች የእያንዳንዳችንን መታወቂያ በዝርዝር እያዩ፤ 'የወሎ መታወቂያ የያዛችሁ ወደመጣችሁበት ተመለሱ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም' አሉን" በማለት ይናገራል።

ይህ ነዋሪ በሸኖ በኩል ወደ አዲስ አበባ መግባት ባለመቻሉ፤ በምንጃር ሸንኮራ በኩል ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ይናገራል።

"70 ወይም 80 የሚሆን መኪና ነው ወደ ደብረ ብርሃን የተመለሰው። አሁን በደብረ ብርሃን እንገኛለን" በማለት ያስረዳል።

ሌላኛው የደሴ ከተማ ነዋሪ፤ ሸኖ ከተማን አልፎ ለገጣፎ ከደረሰ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች እንዲመለስ መደረጉን ይናገራል።

"እንደ ኢትዮጵያዊ ያለውን ችግር የትም ሄደን ማሳለፍ እንደምንችል እናምናለን። የአዲስ አበባ ነዋሪ ያልሆናችሁ 'ወደ መጣችሁበት ተመለሱ' አሉን። አሁን ደብረ ብርሃን ነን" ብሏል።

የቂምቢቢ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ነጋሽ ከጦርነቱ በመሸሽ ከሰሜን የአገሪቱ ክፍል ተነስተው አዲስ አበባ ለመግባት ጥረት ከሚያደርጉት መካከል ወታደሮች እንደሚገኙበት ይናገራሉ።

ወታደሮች የሆኑት በመከላከያ ሠራዊት ትጥቅ እንዲፈቱ እየተደረገ ሕክምና የሚፈልጉትን ወደ ሕክምና ቦታ የተቀሩትን ደግሞ ወደ አማራ ክልል እንዲሄዱ መደረጉን ጨምረው ገልፀዋል።

ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ከተማቸው የመጡ ሲቪሎችን በተመለከተም፤ "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጥተዋል። አምስት አባላት ያለው ቤተሰብ ተፈናቅሎ መጥቷል። ከሰዉ ባሻገር ወደዚህ አካባቢ የመጣው ተሸከርካሪ እጅግ ብዙ ነበር" በማለት አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

"አሁን የሸኖ ከተማ ወደ መረጋጋት ተመልሳለች። በድንበር ላይ ጠንካራ ፍተሻ አለ። ወደ አዲስ አበባ መሄድ የሚችለው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ ያለው ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ የመጣው ሁሉ ወደመጣበት ይመለሳል" ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግሥት ፀጥታ አካላት በትብብር ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረጋቸውን አስተዳዳሪው ጨምረው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ኃይሉ አዱኛ ተፈናቃዮች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እና አስፈላጊ የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ብቻ ናቸው ብለዋል።

"ተፈናቃይ መስለው ለማለፍ የሚሞክሩ አሉ። . . . አጠራጣሪ የደህንነት ጉዳዮች ካስተዋልን ወደ መጡበት እንደሚመለሱ እናደርጋለን" ሲሉ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥብቅ ፍተሻ

ከአማራ ክልል አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በሚደረገው ጥረት በቂምቢቢ ወረዳ ጥብቅ የሆነ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሚገኝ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑን እና የአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ የነዋሪነት መታወቂያ የያዙ ሰዎች አልፈው እንዲጓዙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የወረዳዋ አስተዳዳሪ ሞገስ ነጋሽ፤ በተመሳሳይ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በሁለቱ ክልሎች ድንበር ላይ ጥብቅ ፍተሻ እና ክትትል እየተደረገ ነው በማለት አረጋግጠዋል።

አስተዳዳሪው በዋናው አውራ ጎዳና ላይ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ በመሆኑ አንዳንዶች በገጠራማ መንደሮች አድርገው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውንም ይናገራሉ።

"በሌላ በኩል አድርገው በእግር ለማለፍ ጥረት የሚያደርጉትን የአካካቢ የሚሊሻ አባላት ይቆጣጠራል" ይላሉ። በዚህ መልኩ የተያዙ ሰዎች ወደመጡበት እንደሚለሱ እና ለአገር መከላከያ ተላልፈው እንደሚሰጡ ገልፀዋል።