ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዋግ ኽምራ ዞን ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆኑን ነዋሪዎችና ኃላፊዎች ገለፁ
በአማራ ክልል በሚገኘው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በርካታ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ መሆኑን ከአካባቢው ወደ ባሕር ዳር እና እብናት የመጡ ነዋሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ የአካባቢው ማኅበረሰብ ላለፉት አራት ወራት ምንም ዓይነት እርዳታ አግኝቶ እንደማያውቅ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና ከተማ ሰቆጣን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ከተሞች በህወሓት አማፂያን ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው በብዛት ኑሮውን በእርዳታ የሚደጎመው የአካባቢው ማኅበረሰብ ካለፈው ዓመት ሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላገኘ ጨምረው ተናግረዋል።
የዛሬ ዓመት በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከተስፋፋ ጀምሮ አብዛኞቹ ወረዳዎች ለሰብዓዊ እርዳታ ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አካባቢውን ከላሊበላም ሆነ ከሰቆጣ የሚያገናኘው መንገድ ከሐምሌ 09/2013 ዓ.ም ጀምሮ በመዘጋቱ ሰብዓዊ እርዳታም ሆነ የመድኃኒት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ።
በዚህም ምክንያት በርካታ የአካባቢው ሕዝብ ለከፋ ችግር መዳረጉን፣ ብዙ ሰዎችም በረሃብ እየሞቱ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ኃላፊዎች ይናገራሉ።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ የምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ኮሚሽን፣ በክልሉ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ ከሆነ የህወሓት አማፂያን በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ከ110 በላይ እናቶች፣ ሕጻናት እና ተመላላሽ ታካሚዎች በምግብ፣ በውሃ እና በመድኃኒት እጦት ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ኮሚሽኑ በአካባቢው የመንግሥት መዋቅር በመፍረሱ ምክንያት በምግብ እና በህክምና እጦት የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርን ማወቅ አለመቻሉን ገልፆ፣ ከዚህም ሊጨምር ይችላል ብሏል።
የህወሓት አማፂያን በተቆጣጠሯቸው ዞኖች እንዲሁም ከእነዚህ አካባቢ ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ሰዎች ለምግብ፣ ለመጠጥ ውሃ እና የመድኃኒት እጦት ተጋልጠዋል ሲል ኮሚሽኑ ጨምሮ ገልጿል።
አክሎም በሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ከፊል ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ዋግ ኽምራ ውስጥ የሚኖሩ እና ተፈናቅለው የሚገኙትን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግሯል።
'. . .ችላ ተብለናል'
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ገብሬ አካባቢውን የህወሓት አማፂያን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ይናገራሉ።
"የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የችግሩን አሳሳቢነት ብናሳውቅም ማንም ሊደርስልን አልቻለም። . . .ችላ ተብለናል" ብለዋል።
ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 50 ሺህ የሚጠጉ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ ነዋሪዎች በአንጻራዊነት ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ ቢሆንም እነሱም በችግር ውስጥ መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ወደ 635 ሺህ ሕዝብ ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተጋልጧል ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በረብ ሞተዋል ስለሚባሉት ሰዎች መረጃው ቢኖራቸውም ቁጥሩ ግን ከሚገለጸው በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበረ ቢሆንም የህወሓት አማፂያን ወደ አካባቢው መግባታቸውን ተከትሎ ምንም አይነት እርዳታ ደርሶ እንደማያውቅ ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወንድሙ ወዳጅ ሰሞኑን ወደ ባሕር ዳር ከመጡት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ረሃብ በመከሰቱ በአሁኑ ወቅት ከአቅመ ደካሞች ውጪ አብዛኛው የወረዳው ነዋሪ ሰብዓዊ እርዳታ ፍለጋ አካባቢውን ለቅቆ እየተሰደደ ነው።
"ቤተሰብ ቢያንስ ልጆቼ ቢተርፉልኝና እርዳታ ቢያገኙ እያለ ልጆቹን ወደ እብናት እና ባሕር ዳር ይልካል። ነገር ግን እዚህም እርዳታ የለም" ብለዋል።
በረሃብ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ወንድሙ፣ በወረዳው 21 ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ቀበሌዎች በየቀኑ ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ሰው በረሃብ ምክንያት እንደሚሞት ይናገራሉ።
"እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ሰው ያለውን እየተበዳደረ ይመገብ ነበር፣ ከጊዜ በኋላ ግን አንዳንድ አቅመ ደካሞች የበለጠ በመቸገራቸው ወጣቶች ቤት ለቤት እየለመኑ፣ በጣም የተራቡትን እየመረጥን እንደጉማቸው ነበር። ነገር ግን አሁን ትተናቸው በመምጣታችን ይሙቱ ይኑሩ አናውቅም" ብለዋል።
በዚሁ ወረዳ [ጋዝጊብላ] የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን መዓዛ፣ በወረዳው ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በወረዳው በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች በመገኘት መረጃ ለማጠናቀር አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፣ ቢያንስ እርሳቸው የሚያውቋቸው ሦስት ሰዎች በርሃብ ምክንያት ሕይወታቸው አልፎ በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ተገኝተዋል።
በወረዳው ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ሲሆኑ አብዛኞቹ የመጨረሻ ሰብዓዊ እርዳታ ያገኙት ከግንቦት ወር በፊት መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን፣ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ቢያንስ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑት የከፋ ችግር ውስጥ ስለነበሩ እጅግ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር ብለዋል።
ነገር ግን ወዲያውኑ ጦርነቱ በመከሰቱ ምንም አይነት እርዳታ ሳያገኙ መንገዶቹ ተዘጋግተዋል ብለዋል።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባታቸውን ተከትሎ የመብራት፣ ውሃ እና ባንክ የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው እና የንግድ ልውውጥ ባለመኖሩ ችግሩን የከፋ እንዳደረገውም ይናገራሉ።
በዚህም ምክንያት የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት ከመከሰቱም በላይ የዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ሆኗል የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ለአብነትም የአንድ ኪሎ ጨው ዋጋ እስከ 100 ብር መድረሱን ይናገራሉ።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ በረሃብ ከሚሞተው ሕዝብ በተጨማሪ ". . . በንጹሃን ዜጎች ላይ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል እና መረጃ አምጡ በማለት በርካታ ሰዎች በህወሓት ተገድለዋል" ሲሉ ይከስሳሉ።
ቢቢሲ በአካባቢው የህወሓት ኃይሎች ፈፀሙት ስለተባለው ግድያ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በአጠቃላይ እስከ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ቀውስ ሊጋለጡ ይችላሉ ማለቱ ይታወሳል።
ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለረሃብ አደጋ ሲያጋልጥ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል ይላል።