በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ተሳትፈውበታል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

በአማራ ክልል ወሎ ውሰጥ በተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ተዋጊዎች ጎን ሆነው ተዋግተዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሚኒስትሮች እንዲሁም ከሚኒስቴር ዴኤታዎች ጋር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የተመለከተ ማብራሪያ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 21፣ 2014 በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

በአማራ ክልል የሚገኙት ደሴ እና ኮምቦልቻ በትግራይ አማፂያን መያዛቸው ከተዘገበ በኋላ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ከተሞች ላይ በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ እና የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው ነጮች እና ጥቁሮች መሳተፋቸውንም ገልጸዋል።

"በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ተሳትፈውበታል፤ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ እና የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው ሰዎች ተሳትፈው መስዋዕትነት ከፍለዋል። ነጮች እና ጥቁሮች ከህወሓት ጋር በመሆን ተሳትፈው ሞተዋል" በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝር ጉዳይ ሆነ መረጃም ከማቅረብ ተቆጥበዋል።

ህወሃት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ውድቅ አድርጎታል።

በዚህ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ተቀድቶ በተላለፈው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ጦርነቱን አሁንም የማዕከላዊው መንግሥት እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

«ምንም ጦርነት ሳናደርግ ይህንን ሃይል ብንቀበለው፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንትናውን ህወሓት ሳይሆን የዘመነውን ህሓሃት ለመሸከም ጫንቃዋ አይችልም» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። «አሁን ማሸነፍ መሸነፍ ሳይሆን እኩይ አላማው የሚሳካበት ጭላንጭል መንገድ የለም፤ የኢትዮጵያ አውድ ተቀይሯል። ከተቀየረው የኢትዮጵያ አውድ ጋር መቀየር የሚችል ኃይል አይደለም» ሲሉ ደምድመዋል።

የጦርነቱ ዋና አላማም የተፋላሚ ባላንጣቸውን «የፖለቲካ አላማ እና የቁስ ትጥቆችን በማስፈታት ሰላም ማምጣት» እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። «በትጥቅ ኃይል መንግሥት የመፍጠር ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው ማድረግ ነው» ሲሉ ሌላው የጦርነቱ አላማ እንደሆነም ተናግረዋል።

ዐቢይ አክለውም «የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳግም ባርነት፥ ዘረፋ እና ለዳግም ከፋፍለህ ግዛ እሳቤ ዝግጁ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጧል። ይህንን ገንዘብ በማዋጣት፥ በተወሰነ ደረጃ ልጆቹን በመስጠት ብሎም በሰልፍ አረጋግጧል። ግን በቂ አይደለም» ሲሉም ተናግረዋል። «በሆያ ሆዬ በጥይት የተደራጀ ቡድንን አንመልስም። በተደራጀ መንገድ እንጂ» ሲሉም አክለዋል።

ሕዝቡ በተቀሰቀሰው ልክ በመንግሥት አደረጃጀት መስራት የሚገባው ስራ በቂ አልነበረም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅሰዋል። «ሆ ብሎ የወጣው ሰው ከሶሰት ቀን በኋላ ውሃ ሲጠማው ሆ ብሎ ተመለሰ» ብለዋል። የአማራ ክልልን ጨምሮ ክልሎች እየወሰዱ ያለው እርምጃም ይህንን ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን ምክክር ተከትሎ በተደረሰ መደምደሚያ መሰረት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ብሎም በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የሆነው በወሎ ግንባር ተሳትፈዋል ያሏቸው «የውጪ ዜጎች» ጉዳይ ነው። «የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው፤ ነጮች ጥቁሮች ከህወሓት ጋር ተዋግተው መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ሞተዋል። እኛ ካለን የቴክኖሎጂ አቅም በላይ ያላቸው ኃይሎች በቴክኖሎጂ እና በመረጃ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋሉ» ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝቡ እንዲሁም በሚኒስትሮቹ ውስጥ ያለውን ስጋት እንደሚገነዘቡ እና ይህንን የሚመጥን የመቀልበስ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ስለ ጦርነቱ ሁኔታዎች ሲያስረዱም የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ለቅቆ ከወጣ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ውጊያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል። ከአስር ቀን በፊት ህወሓት «ፈንጂ ደርድሮ በሌላ መንገድ ለማጥቃት መምጣቱን እና ፈንጂውን ለወታደሩ ለማጽዳት 19 ወጣቶች በፈንጂው ላይ ተንከባለው አጥርተው አሳልፈዋል» ሲሉ ገልጸዋል።

ውጊያዎች አንዳንዴ ማሸነፍ አንዳንዴ መሸነፍ ቢኖርም የጦርነቱ አጠቃላይ አሸናፊ ግን የማዕከላዊ መንግሥቱ እንደሚሆን እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

«አቅማችን አልተነካም» ያሉት ዐቢይ «እንኳን የኢትዮጵያ እዚህ ያላችሁ የእናንተ አቅም እንኳን አልተነካም» ሲሉ ለሚኒስትሮቹ ተናግረዋል። «ይህንን አቅም ሰብስበን አሁን በቅርብ ከምናያቸውም ሆነ በርቀት ከምንሰጋቸው ጠላቶች ኢትዮጵያን መታደግ ይቻላል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለዚህም ስራ መሰራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ሚኒስትሮች በአንድ በኩል የዕለት ተዕለት ስራ ብሎም ተጨማሪ የስራ ሰዓት በመጨመር መከላከያን ወደ ማሰልጠኛ በመሄድ ስልጠና እንዲሰጡ አሳስበዋል።

«አዲስ አበባ ሆነው የጠላት አፍ ሆነው ሕዝባችንን ትጥቅ የሚያስፈቱ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። እሱን ከክልሎች ጋር ተነጋግረናል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። እዚህ ያላችሁም አስፈጽሙት። አሉ እንደዚህ የነጻ ሚዲያን በማስመሰል የሚጫወቱ አሉ። ነጻነት በአገር ቀልድ አይሰራም። ብዙ ድራማዎች አሉ። እርሱ ላይ ጠንከር ያለ ነገር ይወሰዳል» ሲሉም አስጠንቅቀዋል።