የትግራይ ተዋጊዎችና የኦሮሞ ነፃነት ጦር መገናኘታቸውን የህወሓት ቃል አቀባይ አስታወቁ

የትግራይ ተዋጊዎች የኦሮሞ ነፃነት ጦር ጋር መስመር ላይ መገናኘታቸውን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ገለጹ።

አብረው ውጊያ ጀምረዋል የሚለው ላይ ግን አቶ ጌታቸው ምንም አስተያየት አልሰጡም።

ቀደም ብሎ የኦሮሞ ነፃነት ጦር አዛዥ ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮ ሁለቱ ታጣቂ ኃይሎች በቅርብ ቀናት ውስጥ ለሁለቱም ቀረብ ባሉ አካባቢዎች ጎን ለጎን ውጊያ እንደሚጀምሩ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጃቸው ህወሓትና የኦሮሞ ነፃነት ጦር (ሸኔ) አብረው ለመስራት የተስማሙት ከሁለት ወራት በፊት ነው።

ህወሓትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት አንጻር በወታደራዊ መስክ ለመተባበር መስማማታቸውን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በአሁኑ ወቅት የጦሩ መሪ ጃል መሮ በመጪዎቹ ቀናት ለመጀመሪያ ጊዜ ጎን ለጎን ሆነው አብረው እንደሚዋጉና መዲናዋን አዲስ አበባን ለመቆጣጠር የመጨረሻ ግፊት እንደሚያደርጉም ገልጿል።

በተያያዘ ዜና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር መሪ ተዋጊዎቻቸው በምዕራብ፣ በማዕከላዊ እና በደቡብ ኦሮሚያ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተዋጊዎቻቸው እያፈገፈጉ ከነበሩት የመንግሥት ኃይሎ ች የገጠማቸው ተቃውሞ ትንሽ እንደነበር አክሎ ገልጿል።

የጦሩ መሪ ኃይላቸው ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየተቃረበ እንደሆነና በምዕራብ ኦሮሚያ የምትገኘውንም ወለጋንም መቆጣጠራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የዓይን እማኞች በአካበቢው የሚገኙ መንገዶች እንደተዘጉና የአማፂው ታጣቂዎችም የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን እያዋከቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዋናው ከተማው በስተምዕራብ 250 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጂባት አንዳንድ አካባቢዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ጃል መሮ እንዳለው ወረዳውን እንዳልተቆጣጠሩት ገልጸዋል።

ቢቢሲ ይህንን አስመልክቶ የመንግሥት ቃለ አቀባይን ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት የፌደራል ኃይሎች እና አጋሮቻቸው የበለጠ ኪሳራ እንደደረሰባቸው እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው የኦሮሞ ነፃነት ጦር አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ያሳወቀው።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር ተቆጣጥሬያቸዋለሁ የሚላቸውን ስፍራዎች የስልክና ኢንተርኔት ግንኙነት ባለመኖሩ በተናጥል ማረጋገጥ ከባድ ነው።

ጃል መሮ በሳምንቱ መጨረሻ አዳዲስ ከተሞችን እንደያዙ ከተነገረላቸው ከትግራይ ታጣቂዎች ጋር ጦርነቱን በአንድ ላይ እንደሚዋጉም ተናግሯል።

በሳምንቱ መጨረሻ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ደሴንና የኮምቦልቻ ከተማንና የአየር ማረፊያዋን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከዚህም በተጨማሪ እሁድ ምሽትም የኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር ከኮምቦልቻ 53 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ከሚሴን መቆጣጠራቸውን ሮይተርስ ጨምሮ በዘገባው አስነብቧል።

ከመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በኩል በደሴ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረጉን ቢገልፁም የትግራይ ተዋጊዎች ተቆጣጥረውታል የሚለውን አስተባብሎ ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ዜጎች 'የክት' ጉዳያቸውን አቁመው "ህወሓትን 'ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሳሪያ እና አቅም ይዞ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።