በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት ቆመ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያ መሰጠት ማቆሙን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

በዚህም መሠረት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የወረዳ አስተዳደሮች በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያየዘ የነዋሪዎች መታወቂያ መስጠት ማቆማቸው ተገልጿል።

ለዚህ ውሳኔ የተሰጠው ምክንያትም በተለያዩ መንገዶች ወደ ከተማዋ የሚገቡ "ፀጉረ ልውጦችን እና ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል" እና የሕዝቡን ድኅንነት ለመጠበቅ ሲባል እንደሆነ በከተማዋ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪ በኩል ተገልጿል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን እና ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

ይህ "በአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014" የባለው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ የተለያዩ ክልከላዎችንና ግዴታዎችን የያዘ ሲሆን ከእነሲህም ውስጥ ዜጎች ማንነታቸውን የሚገልጽ ሕጋዊ መታወቂያ እንዲይዙ ያስገድዳል።

በዚህም መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መምሪያ ላይ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ የቀበሌ መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የሠራተኛ መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም ከእነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ በመያዝ እንዲንቀሳቀሱ ያስገድዳል።

አዋጁ የመታወቂያ ሰነዶች የሌለው ሰው በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የፀጥታ እና የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው ደንግጓል።

ከዛሬ ጀምሮ የነዋሪነት በየትኛውም የከተማዋ ወረዳዎች የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት እንዲቆም የወሰነው የአዲስ አበባ መስተዳደርም ነዋሪዎች ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች መታወቂያ ያልወሰዱ ሰዎች በልዩ ሁኔታ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ እና ተረጋግጦ ጊዜያዊ መታወቂያ የሚዘጋጅላቸው እንደሆነ አመልክቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት መስፋፋቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ መስተዳደር የተለያዩ የደኅንነት ጥበቃ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም መካከል የጦር መሣሪያ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በሁለት ቀናት ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው እንዲያሳውቁ ትናንት ጥሪ መቅረቡ ይታወቃል።

የከተማዋ የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) የአዲስ አበባን ሰላም ለማረጋገጥ የጦር መሣሪያ ያላቸው ግለሰቦች በአቅራቢያቸው ባለፖሊስ ጣቢያ በመገኘት እንዲያስመዘገቡ አሳስበዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በሁለት ቀናት ውስጥ በማያሳውቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸውን የመዲናዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ በቀጣይ ቀናት በከተማዋ በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ገልጸው ለዚህም ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።