ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ተወላጆች 'እየተዋከብን ነው' ሲሉ ፖሊስ 'መረጃ የሚገኝባቸውን መያዜን እቀጥላለሁ' አለ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ማንነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ለእስር እየተዳረግን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ የህወሓት ተልዕኮን የሚፈጽሙትን መያዜን እቀጥላለሁ አለ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች፤ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር "ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ ቤታቸው እንደሚበረበር፣ በፖሊስ እንደሚዋከቡ እና አልፎም ለእስር እየተዳረጉ" መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደሚለው ግን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ማንንም የለየ ሳይሆን መረጃን መሠረት በማድረግ የሚከናወን ሕጋዊ መሆኑን አልክቷል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ "ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ነበሩ። በተለይም 22 በሚባለው አካባቢ አፈሳዎች ሲካሄዱ ነበር። በሰሚትና ቡልቡላ አካባቢዎችም የቤት ለቤት ፍተሻዎች እንደሚካሄዱ አውቃለሁ። ይህ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ተቀዛቅዞ ቢቆይም እሁድ ዕለት ግን እንደ አዲስ በተጠናከረ መልኩ ፍተሻው ቀጥሏል" ብለዋል።
ይህ የከተማዋ ነዋሪ የግል መኖሪያ ቤታቸው እንደተፈተሸ እና ቡልቡላ አካባቢ የሚኖሩ የዘመዶቻቸው መኖሪያ ቤትም በፖሊስ መበርበሩን ተናግረዋል።
"ነጻነት የለንም። እንደዚህ ዓይነት የጅምላ አፈሳ ስላሰጋን የትግራይ ተወላጆች በተለይም ወጣቱ ተሳቆ ነው የሚኖረው" በማለት ጨምረው ተናግረዋል።
ሌሎች ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ላይ መታወቂያ እየተጠየቀ መጉላላትና አስር እንደገጠማቸው በመግለጽ ይህንን በመፍራት ከቤታቸው ከመውጣት መቆጠባቸውን አመልክተዋል።
ፖሊስ ባለፉት ቀናት በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች አካሄድኩት ባላቸው ፍተሻዎች የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል።
'እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል'
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ በበኩላቸው "በመዲናዋ የህወሓትን ተልዕኮ የሚፈጽሙ በርካታ ሰዎች አሉ" ካሉ በኋላ፤ በቂ መረጃ የሚገኝባቸውን "እያያዝን ነው። ገና አጠናክረን ነው የምንይዛቸው" ብለዋል።
"[የህወሓት] ተልዕኮ በሚፈጽሙ፤ በሚያስፈጽሙ በቂ መረጃ የሚገኝባቸውን ሰዎችን እየያዝን ነው ወደፊትም እንይዛለን። የትግራይ ተወላጆች ብቻ ባይሆኑም በዋናነት የትግራይ ተወላጆች የሆኑ በዚህ ተግባር የተሳተፉ በርካታ ሰዎች አሉ" ብለዋል።
ኃላፊው እንዳሉት ፖሊስ እርምጃ እየወሰደ ያለው ማንነትን መሠረት አድርጎ እንዳልሆነና በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ የሌሎች ብሔር አባላት ላይም በሚገኙ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ መሆኑን ገልጸዋል።
"ደሴን ወያኔ ተቆጣጠር ሲባል ሲጨፍሩ የነበሩ፤ ፊት ለፊት ሲናገሩ የነበሩ አሉ" ያሉት ኮማንደር ፋሲካው፤ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሰዎችን እያዋለ ያለው ማንነት መሠረት ባደረገ መልኩ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ትናንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚከለክላቸው ተግባራት መካከል፤ "ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት" ሚለው ይገኝበታል።
'በህወሓት ናፋቂዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል'
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመው የደኅንነትና የፀጥታ ግብረ ኃይል "በህወሓት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃ" ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ግብረ ኃይሉ መኖሪያ ቤት ተከራይተው በጋራ የሚንቀሳቀሱ፣ ሰዋራ ስፍራ በመምረጥ ግንኙነት የሚያደርጉ የህወሓት "ደጋፊዎችና ናፋቂዎች" መኖራቸውን ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ፤ መኖሪያ ቤት፣ ንግድ ቤት፣ መጋዘን እና ተሽከርካሪ ያከራዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተከራዮችን ማንነት በጥንቃቄ በማጣራት መረጃውን በአስቸኳይ ለፖሊስ እንዲያሳውቁ አሳስቧል።