ጆ ባይደን ፑቲንንና ሺ ፒንግን ስብሰባ በመቅረታቸው ወቀሱ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያው ፑቲንና የቻይናው ፒንግን ወቀሱ፡፡

ፕሬዝዳንቱ ወቀሳ ያቀረቡት በስኮትላንድ፣ ግላስጎው እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም መንግሥታት ስብሰባ ቻይናና ሩሲያ በመሪ ደረጃ ባለመሳተፋቸው ነው፡፡

የሁለቱ ኃያላን አገራት ተወካዮች በስብሰባው ቢገኙም ፑቲንና ሺ ፒንግ ግን በስብሰባው አለመገኘታቸው ጆ ባይደንን ቅር አሰኝቷል፡፡

ባይደን ማክሰኞ ምሽት ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ትልቁ የዓለም አጀንዳ ነው ያሉ ሲሆን ቻይና ይህን ትልቅ አጀንዳ ቸል ማለቷ፣ ሩሲያውም ለጉዳዩ ትልቅ ቦታ አለመስጠቷ ልክ አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡

የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲንም ሆኑ የቻይናው ሺ ፒንግ በስብሰባው አልተገኙም፡፡ ሆኖም ሁለቱም አገራት ተወካዮቻቸውን ወደ ግላስጎው ልከዋል፡፡

ይህ የዓለም መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን አጀንዳ ያደረገ ግዙፍ ጉባኤ በፈረንጆቹ እስከ ኖቬምበር 14 የሚቆይ ነው፡፡

ቻይና በዓለም በካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት የሚያህላት የለም፡፡ አሜሪካ ሁለተኛዋ አገር ስትሆን፣ ሩሲያ ከአውሮጳ ኅብረትና ከሕንድ ቀጥሎ አምስተኛዋ አገር ናት፡፡

በዚህ የዓለም መንግሥታት ስብሰባ የ120 አገራት መሪዎች በስኮትላንድ ትልቋ ከተማ ግላስጎው ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በርካታ ስምምነቶችን ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትናንት አገራቱ ወሳኝ የሚባል ስምምነት ያደረጉ ሲሆን ይህም የዓለም ዛፍ ምንጣሮን እስከ 2030 በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ መስማማታቸው ነው፡፡

በዚህ ስምምነት ውስጥ ከፍተኛ ምንጣሮ የሚደረግባት የአማዞን ጫካ ባለቤት ብራዚል መኖሯም ትልቅ ስኬት ተደርጎ ተወስዷል፡፡.

ባይደን ይህን የወቀሳ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት የሩሲያው ፑቲን ስብሰባውን በርቀት በመታደም የቴሌቪዥንን ንግግር አድርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከፑቲን ቀጥሎ መድረኩን የተረከቡት ጆ ባይደን ፑቲንና ሺፒንግ በዚህ ስብሰባ አለመገኘታቸው ትልቅ ስህተት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጠዋል፡፡