ዝነኛው የፊልም ተዋናይ በቀረጻ ወቅት ተኩሶ ሰው ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዝነኛው አሜሪካዊ ተዋናይ አሌክ ባልድዊን በፊልም ቀረጻ ወቅት ለቀረጻ ተብሎ የተዘጋጀ መሳሪያ ተኩሶ አንዲት ሴትን ገደለ።
ተዋናይ አሌክ ባልድዊን በፊልም ቀረጻ ወቅት መደበኛ የጦር መሣሪያ ያልሆነ፣ ለፊልም ቀረጻ የሚያገለግል መሳሪያ ከተኮሰ በኋላ አንዲት ሴትን ገድሎ ሌላ አንድ ተጨማሪ ሰው አቁስሏል።
ፖሊስ እንዳለው ባልድዊን መሣሪያውን የተጠቀመው ለሴንቸሪ ዌስተርን ረስት ፊልም በሚቀረጽበት ወቅት ነው።
ጉዳት የደረሰባት ሴት ሆስፒታል ብትወሰድም በደረሰባት ጉዳት ህይወቷ አልፏል። ጉዳት ያጋጠመው የፊልሙ ዳይሬክተር ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።
የተዋናይ ባልድዊን ቃል አቀባይ ለኤፒ የዜና ወኪል እንደተናገረው ክስተቱ የተፈጠው ባዶ መሆን የነበረበት መደበኛ ያልሆነው መሳሪያ በስህተት ከተተኮሰ በኋላ ነው።
ህይወቷ ያለፈው የ42 ዓመቷ ሃልይና ሁትቺንስ የምትባል ሲሆን የፎቶግራፍ ዳይሬክተር ሆና ታገለግል ነበር ተብሏል። ህክምና እየተደረገለት ያለው የፊልሙ ዳይሬክተር የ48 ዓመቱ ዮኤል ሱዛ ነው።
ዝነኛ በሆነው የፊልም ቀረጻ ሥፍራ ቦናንዛ ክሪክ ራንች ስለተፈጠረው ክስተት ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ ሲሆን እስካሁን ምንም ክስ አልተመሰረተም።
የአካባቢው ጋዜጣ ሳንታ ፌ ኒው ሜክሲካን እንደዘገበው የ68 ዓመቱ ባልድዊን ሐሙስ ዕለት እያለቀሰ በአካባቢው የፖሊስ ቢሮ መታየቱን ዘግቧል።
የግል ድረ-ገጿ እንደሚኣሳየው፣ ሟች ሁትቺንስ ከዩክሬን የመጣች ሲሆን ያደገችው በሶቪዬት ወታደራዊ ካምፕ ነው። በኪዬቭ ጋዜጠኝነትን በሎስ አንጀለስ ደግሞ ፊልም ተምራለች። እአአ በ2019 ላይ በአሜሪካ ሲኒማቶግራፈር መጽሔት ተስፋ ያላት ባለሙያ ተብላ ተሸልማ ነበር።
በአዳም ኢጂፕት ሞርቲመር ለሚመራው እና በድርጊት የተሞላ ፊልም ሁትቺንስ ሃልይናን ፊልም፣ የፎቶግራፍ ዳይሬክተር ነበረች።
የዓለም አቀፉ ሲኒማቶግራፈር ጊልድ ለቫሪቲ መጽሔት በሰጠው መግለጫ የሁትቺንስን ሞት "አሳዛኝ ዜና እና አስከፊ ኪሳራ" ብሎታል።
ባልድዊን የፊልሙ ተባባሪ ፐሮዲዩሰር ሲሆን የ13 ዓመት የልጅ ልጁ በድንገተኛ ግድያ የተፈረደበት ግለሰብ ገጸ ባህሪን ይዞ ይተውናል።












