እጥረት የገጠመው የኢትዮጵያ ደም ባንክ ለለጋሾች ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የኢትዮጵያ ደም ባንክ የክምችት እጥረት ስለገጠመው ለጋሾች ደም እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረቡን የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል በንቴ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የደም ባንኩ ያለው ክምችት ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም በተለይ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ መስተዋሉን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት የደም እጥረት ያጋጠመው በደቡብ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሆኑን አቶ ያረጋል ያስረዳሉ።
የደም ባንክ የክምችት እጥረት ያጋጠመው በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት አለመሆኑን አቶ ያረጋል ጨምረው ተናግረዋል።
ጦርነት በሚኖርበት ወቅት የደም እጥረት ማጋጠሙ የተለመደ መሆኑን የገለጹት አቶ ያረጋል፣ እነርሱም እጥረት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።
ነገር ግን ጦርነቱ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ተቀስቅሶ በኅዳር ወር ብቻ 40 ሺህ ደም ለጋሾች ደም መስጠታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በኋላም 'ደሜን ለመከላከያዬ' በሚል በጣም ከፍተኛ የሆነ የደም ልገሳ ዘመቻዎች መደረጋቸውን ጨምረው አብራርተዋል።
ምንጊዜም ከፍተኛ ደም ልገሳ ከተካሄደ በኋላ ባሉት ቀጣይ ወሮች የለጋሾች ቁጥር እንደሚቀንስ ያብራሩት አቶ ያረጋል፣ ጦርነቱ በጣም ከፍተኛ የሆነ የደም ፍላጎት አልፈጠረብንም ብለዋል።
ጦርነቱ እየተካሄደ ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ደሴ፣ ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ መተማ እና ደብረታቦር ላይ እጥረት አለመኖሩን ገልፀዋል።
አክለውም በሐረር ያለው የደም ልገሳ ልማድ አነስተኛ መሆኑን በማንሳት፣ በደቡብ ክልል ግን ደም ለጋሾችን በቀላሉ ለማግኘት ሁሉ ነገር ምቹ ቢሆንም በቂ ሥራ አለመሰራቱን ያስረዳሉ።
ግጭቱ የደም ፍላጎት ቢፈጥርም "በራሱ ግን የፈጠረው እጥረት የለም" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ይህም የሆነው በአካባቢው ያለው ኅብረተሰብ 'በነቂስ ወጥቶ በመለገሱ' የአካባቢው የደም ባንኮች አቅርቦቱን በራሳቸው መሸፈን በመቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በአማራና በኦሮሚያ ክልል በእያንዳንዳቸው 10 የደም ባንኮች ይገኛሉ።
በትግራይ ክልል ሦስት፣ በአፋር ሁለት፣ በሶማሌ ሦስት፣ በቤንሻንጉል ሁለት፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ደግሞ አንድ አንድ የደም ባንኮች ሲኖሩ ይህም ቁጥሩን በአገር አቀፍ ደረጃ 43 አድርሶታል።
እነዚህ 43 ደም ባንኮች ከለጋሾች ደም ሰብስበው በመመርመር ለሚፈልጉ የህክምና ተቋማት እንደሚያከፋፍሉ አቶ ያረጋል ይናገራሉ።
የደም ክምችት እጥረት አጋጠመ?
በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ ሰዎች መካከል ሁለት ወይንም ሦስት ሰዎች ብቻ ደም እንደሚለግሱ የገለፁት አቶ ያረጋል፣ የእነዚህ ሰዎች በሐምሌ እና በነሐሴ ወር ደም መለገሳቸው በመስከረም ላይ ክፍተት መፍጠሩን አብራርተዋል።
አቶ ያረጋል በመስከረም ወር ለምን የደም ክምችት እጥረት እንደሚያጋጥም ሲያስረዱ፣ ትምህርት ቤቶች ዘግይተው መከፈታቸው፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መጠናቀቅ ምክንያት መሆናቸወን ያነሳሉ።
ከጳጉሜን ወር ጀምሮ ኅብረተሰቡ በዓል ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአገር አቀፍ እንዲሁም በአዲስ አበባ በነበሩ ትልልቅ ዝግጅቶች ምክንያት ኅብረተሰቡ ሙሉ ትኩረቱን በዓላት ላይ በማድረጉ ደም ለመለገስ አለመምጣቱን ጠቅሰዋል።
እንዲህ አይነት የደም ክምችት እጥረት በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የሁለት ወር ሁዳዴ ጾም ላይ በሚሆኑበት ወቅት እንደሚያጋጥምም አቶ ያረጋል ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ግን ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ የክምችቱ እጥረት ወደ ጥቅምት ወር መሸጋገሩን ጨምረው ገልጸዋል።
አሁን ያለው እጥረት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ እና ችግሩ በፍጥነት ካልተፈታ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ "ከፍተኛ የሆነ ቀውስ" ሊያጋጥም እንደሚችል ስጋት አላቸው።
አሁን ያለው ክምችት "በእርግጠኝነት ከአንድ ሳምንት በላይ አያስኬድም" ያሉት አቶ ያረጋል፣ ይህ ማለት ግን አንድ ሳምንት ሙሉ ምንም ደም ከለጋሾች ሳንወስድ ከቀረን ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ጨምረውም የደም ባንኩ ምንጊዜም በዛ ከተባለ የአራት ሳምንታት የደም ክምችት እንደሚይዝ ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደም የመለገስ ባህል
ከሦስት ዓመት በፊት ሰኔ 15/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ለደም ባንክ 'ትልቅ አብዮት' ማስነሳቱን በመጥቀስ፣ 'ወሳኝ ዕለት' እንደነበር አቶ ያረጋል ያስታውሳሉ።
በወቅቱ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ ለቆሰሉ ሰዎች ደም ለመለገስ የተፈጠረው ንቅናቄ፣ በርካታ ለጋሾችን ወደ ደም ባንክ ማምጣቱን አክለው ገልጸዋል።
ከዚያ ዕለት ጀምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአምስት ተከታታይ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ያስታወሱት አቶ ያረጋል፤ በመሪ ደረጃ ደም መለገስ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ለጋሽ በአንድ ጊዜ ማግኘት በደም ባንክ ታሪክ ውስጥ ተፈጥሮ እንደማያው ጠቅሰዋል።
የሕብረተሰቡ በበጎ ፈቃደኝነት ደም መለገስ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም በማስረጃ አስደግፈው ሲያስረዱ፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የደም ክምችት እጥረት በርካታ አገራትን ሲፈታተን ከፍተኛ ደም በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከብሩንዲ በመቀጠል ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደነበረች ገልጸዋል።
አዳዲስ ደም የመለገስ ልምምድ እያዳበሩ ያሉ ሰዎችን መደበኛ ደም ለጋሽ በመሆን እንዲቀጥሉ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ግን አስታውሰዋል።
በ2013 ዓ.ም ብቻ 288 ሺህ ደም ሲሰበሰብ፣ በጣም በርካታ ሰው ደም የሰጠው ደግሞ በኅዳር ወር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ምንም እንኳ የዓለም ጤና ድርጅት በዓመት አንድ ሚሊዮን ደም እንዲሰበሰብ ቢመክርም ኢትዮጵያ ግን በዓመት 300 ሺህ ያህል ደም ከለጋሾች እንደምትሰበስብ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
ይህ ለምን እንደሆነ አቶ ያረጋል ሲያስረዱም በኢትዮጵያ ያለው የደም ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑን ነው ይላሉ።
በተጨማሪም ሕክምናዎች ባለመስፋፋታቸው መሆኑን በመግለጽ የካንሰር ሕክምና አለመስፋፋት፣ በዓመት የሚደረጉ የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የደም ፍላጎቱ አነስተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት አንጻር ስትታይ በደም ለጋሾች ቁጥርም ሆነ በሚሰበሰብ ደም ብዛት መጠን የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አቶ ያረጋል ተናግረዋል።
አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ እና ኢትዮጵያ ብቻ በበጎ ፈቃደኝነት ደም የሚለግሱ ሰዎች የሚገኙባቸው ሲሆኑ በቀሪዎቹ አገራት ግን ከቤተሰብ በሚሰጥ ምትክ ደም ይጠቀማሉ።















