ደም ልገሳ፡ በቴክኖሎጂ ታግዞ ለጋሾችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነው የባሕር ዳር የደም ባንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም።
ባሕር ዳር። ዝናባማው ነሐሴ 1/2008 እንደ ሌሎቹ የክረምት ቀናት አልነበረም።
ውጥረት ነግሷል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ጎንደር የነበረው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ባሕር ዳር ደርሷል።
እኩለ ቀን ከመሆኑ በፊት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የተኩስ ድምጽ ይሰማል።
አባይ ማዶ ቤዛዊት ቤተ መንግሥት መገንጠያ በሚባለው አካባቢ ደግሞ ነገሮች ተጋግለዋል።
ጥይት ከየአቅጣጫው ይተኮሳል።
በጸጥታ አካላት ህይወታቸውን ያጡ ነበሩ። ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጤና ተቋማት ያቀኑትም ቁጥር ጥቂት አይደለም።
ከተጎጂዎች ጋር ሆስፒታል ከደረሱት መካከል የባሕር ዳር ነዋሪው ሄኖክ ዳኘው ይገኝበታል።
"በዕለቱ ከፍተኛ የደም እጥረት ነበር" ይላል ሄኖክ የነበረውን ሲያስታውስ።
የባሕር ዳር ደም ባንክ የደም እጥረት የሚገጥመው ዓይነት አልነበረም።
ክረምት ሲሆን ግን ሁኔታው ይቀየራል።
ምክንያት? ምክንያትማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሉም።
ለደም ባንኩ ቀዳሚዎቹ ለጋሾች አነዚህ ተማሪዎች ናቸው። እነሱ ከሌሉ የደም እጥረት ይኖራል። ለዚያውም እንደዚህ ደም በብዛት በሚያስፈልግበት ወቅት።
"የከተማው ነዋሪ ደም የመስጠት ልማድ አልነበረውም" ይላል ሄኖክ። የእሱም ከዚህ የተለየ አልነበረም።
ችግር ምን የማይቀይረው ነገር አለ?
ሄኖክም የተጎዱትን ለመርዳት ደም ለገሰ።
በእኔ ይብቃ አላለም። ደም መለገስ ብቻ ሳይሆን የከተማዋ ነዋሪም ደም በመለገስ እንዲሳተፍ ማነሳሳት ጀመረ።
2012
ደም ከለጋሶች ለማግኘት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ከለጋሾች "ደማችን ከምን ደረሰ?" የሚል ጥያቄ ይነሳል የሚሉት ደግሞ የባሕር ዳር ባንክ ኃላፊ አቶ ምክሩ ናቸው።
የነበረው የመረጃ ሥርዓት ኋላ ቀር ነው። የደም ለጋሾችን ጥያቄም አይፈታም።
ጥያቄውን ለመፍታት ማማተር ተጀመረ።
ደቡብ አፍሪካ ስልክ በመደወል አውሮፓ ደግሞ በጽሑፍ መልዕክት ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር መኖሩ ታወቀ።
ባህር ዳርስ ምን ይሠራ?
በጉዳዩ ላይ ከደም ለጋሾች ጋር ሲወያዩ 'ኤርሚያስ የሚባል ባለሙያ ስለጉዳዩ እያሰበበት እንደነበር' ለአቶ ምክሩ ይነግራቸዋል።
በጋራ መረጃዎች ተገላበጡ። ጥናቶች ተከናወኑ።
የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ እና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት ከውሳኔ ተደረሰ።
ዋጋው ግን የሚቀመስ አልሆንም።
በክልሉ ድጋፍ እና በበጎ ፈቃኞች ትብብር ግን ከግብ ደረሰ።
በ2012 ዓ.ም የባሕር ዳር የደም ባንክ የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ እና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በመጠቀም በኢትዮጵያ ካሉ 40 የደም ባንኮች ቀዳሚው ሆነ።
የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ እና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ የሚጀምረው "አንድ ሰው ደም ከለገሰ በኋላ ደሙ የደም ባንክ መድረሱን በጽሑፍ መልዕክት ለለጋሾች ያሳውቃል" ይላሉ አቶ ምክሩ።

አጭር የጽሑፍ መልዕክቱ በዚህ ብቻ አያበቃም።
ቀጣይ ደግሞ የለጋሾች የደም ዓይነትን የሚገልጽ ጽሑፍ ወደ ለጋሾች ተንቀሳቃሽ ስልክ ያደርሳል።
"የጉበት፣ የኤችአይቪ፣ የአባላዘርና የሌሎች በሽታዎች ምርመራ [በተሰበሰበው ደም ላይ] ከተከናወነ በኋላ ለጋሾች ውጤታቸውን ቢሮ ድረስ መጥተው እንዲወስዱ መልዕክት ያደርሳቸዋል" ይላሉ።
ደም ለጋሾች ደም ባንኩ ድረስ በመሄድ ውጤታቸውን ይወስዳሉ።
ቀጣዩ ደግሞ ደም ለሚፈልጉ ሰዎች የሚሆነው ደም ይለያል።
የባሕር ዳር የደም ባንክ ወደሚያስፈልጋቸው የጤና ተቋማት ደሙን ይልካል።
ለደም ለጋሾች ደግሞ "ውድ ደም ለጋሻችን [የለጋሹ ስም አለ] የለገሱት ደም [የሆስፒታሉ ስም] ደርሶ የሦስት ሰዎችን ህይወት ታድጓል። እናመሰግናለን። የባሕር ዳር ደም ባንክ" የሚል መልዕክት ይደርሳል።
ከደም ለጋሾች ጋር ያለው የመረጃ ልውውጥ በዚህ አያበቃም።
ከሦስት ወር በኋላ ደም ለጋሾች በድጋሚ ደም መለገስ እንደሚችሉ የሚገልጽ የማስታወሻ መልዕክት ይደርሳቸዋል።
"ውድ ደም ለጋሻችን [የለጋሹ ስም አለ] ደም ከለገሱ ሦስት ወር ስለሞላዎት መጥተው መለገስ ይችላሉ። እናመሰግናለን። የባሕር ዳር ደም ባንክ" ይላል።
"የጽሑፍ መልዕክቱ የእውነትም ያነሳሳል። በየጊዜው ያለህበትን የጤና ሁኔታ ያሳውቃል" ይላል ሄኖክ።
የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ ለደም ባንኩ ከዚህም በላይ ነው።
"በዚህ ዘዴ ለተመረጡ የደም ዓይነቶች ብቻ መልዕክት ለመላክ ያስችላል። የትኛው የደም ዓይነት በየትኛው አካባቢ በብዛት እንደሚገኝ ያሳውቃል" ይላሉ አቶ ምክሩ።
ይህ ደግሞ የደም ባንኩ ውሳኔዎች ላይ በቀላሉ ለመድረስ አግዞታል።
ከ11ሺህ ወደ 20ሺህ
አዲሱ አሠራር የደም ባንኩን ብዙ ጠቅሞታል።
"ቀደም ሲል ደም ለታካሚዎች የሚሰጠው ከቤተሰቦቻቸው በሚገኝ ምትክ ደም ነበር። አንዳንዶችም ሌሎች እንዲሰጡላቸው ይከፍሉ ነበር። ይህ አሠራር አሁንም ያለ የሚመስላቸው አሉ" ይላሉ አቶ ምክሩ።
አዲሱ አሠራር ግን ከዚህ በተቃራኒ ለጋሾች በደም ባንኩ ላይ እምነታቸውን እንዲጥሉ አድርጓቸዋል እንደ ኃላፊው ከሆነ።
ደሙ የደረሰበትን ከማሳወቅ ሌላ ወደየትኛው ሆስፒታል እንደደረሰ ስለሚያሳውቅ ነው ይህን ማለታቸው።
እንደባንኩ ሁሉ ደም ለጋሾችም በአሠራሩ ረክተዋል።
"የት ሆስፒታል ደሜ እንደተሰጠ ሳውቅ። ደም የመስጠት ሞራልን ያነሳሳል። ደም በመለገስ የተጨማሪ ሰዎችን ህይውት እንዳድን የበለጠ ሞራል ይሰጣል" ይላል ሄኖክ።

የፎቶው ባለመብት, Mikhail Tereshchenko
በ2011 የባሕር ዳር የደም ባንክ በዓመት 11 ሺህ ደም ለጋሾች ነበሩት። በወቅቱ የጽሑፍ መልዕክቱ አሰራር አልተተገበረም ነበር።
በ2011 ተግባራዊ ተደረገ። የደም ለጋሾች ቁጥር 20 ሺህ ደረሰ።
"ዘንድሮም ቁጥሩ [ከወዲሁ] 24 ሺህ ደርሷል። ደም ለጋሾች [የምርመራ] ውጤታቸውን የመቀበላቸው ምጣኔም ጨምሯል" ይላሉ አቶ ምክሩ።
"ኡ ኡ ኡ ስሜቴን መግለጽ በጣም ይከብዳል። መልዕክቱ ሲደርስ በጣም ደስ ይላል። ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። ይህ ከቁሳዊ ሃብትም በላይ ነው" ይላል ሄኖክ የሦስት ሰው ህይወት ስለመታደጉ የሚደርሰውን መልዕክት ሲያገኝ ያለውን ስሜት ተጠይቆ ሲመልስ።
ሦስት-በሽልማት ላይ ሽልማት
በኢትዮጵያ ከ40 በላይ የደም ባንኮች ይገኛሉ።
ይህንን አሠራር ተግባራዊ ያደረገው ግን የባሕር ዳሩ የደም ባንክ ብቻ ነው።
አዲስ አበባን ጨምሮ ካሉት የደም ባንኮች 160 በመቶ ደም በማሰባሰብ ቀዳሚ ሆኗል።
"አምና ሦስት ሽልማት ወስደናል" ይላሉ ኃላፊው። የመጀመሪያው ባሕር ዳር ከሚገኙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች 'ለከተማው ጥሩ የሠራ' በሚል በኅብረተሰቡ ተመርጦ ተሸልሟል።
ሁለተኛው ሽልማት ከክልሉ ነው።
የክልሉ ጤና ቢሮ የባሕር ዳር የደም ባንክ ባስመዘገበው አፈጻጸም ከክልሉ ቀዳሚ በማለትም በድጋሚ ሸለመው።
ሦስተኛው ሽልማት በአገር አቀፍ ደረጃ ነው።
ብሔራዊ የደም ባንክ ስር ካሉት ባንኮች ቀዳሚው በመሆን ሦስተኛውን ሽልማት በማግኘት 'ሃትሪክ' ሠራ።
የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ እና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በባሕር ዳር የደም ባንክ ብቻ እንዲወሰን አልተፈለገም።
በአማራ ክልል 10 የደም ባንኮች ይገኛሉ።
ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ወልዲያ፣ መተማ እና ደብረ ማርቆስ የመረጃ አያያዙን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።
በቀጣይ ደግሞ የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎቱን ይተገብራሉ።
ቀሪዎቹም በክልሉ የሚገኙ የደም ባንኮች በዚሁ መልክ መሥራት ከጀመሩ በኋላ ትኩረቱ ወደ አገር አቀፍ ይሆናል።
እዚህ ለመድረስ መውጣት መውረድ ነበር።
"ተስፋ የሚያስቆርጡ ጊዜዎች ነበሩ። አብረውን የሚሠሩት ጭምር የማይመስል ነገር ነው ይሉ ነበር። ተስፋ የሚሰጠውም ጊዜ እየመጣ ለዚህ ደርሰናል" ይላሉ አቶ ምክሩ።
"በቀጣይ የጤና ሚንስቴር አሠራሩን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገብር እንፈልጋለን። ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል የነበሩት አመራሮች የገቡትን ቃል ወደ ተግባር ተለውጦ ማየት" ምኞታቸው ነው።
150 አዲስ ለጋሾች
ሄኖክ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደም ከአስር ጊዜ በላይ ደም ለግሷል።
ደም ከመለገስ ያቋረጠበት ጊዜ የለም።
ዘግይቶ ግን ያውቃል። "'ኢቬንት' ለመጠበቅ ሲል መስጠት ከነበረበት ጊዜ ዘግይቶ የሚሰጥበት ወቅት" መኖሩን ይናገራል።
በታዋቂ ሰዎች (ከሰሞኑ ለአበበች ጎበና መታሰቢያ እንዳደረጉት ዓይነት) እና ታሪካዊ አጋጣሚዎች (የዓድዋ ድል እና የአርበኞች ቀን ተጠቃሽ ናቸው) ምክንያት በማድረግ ነው የደም ልገሳው 'ኢቨንት' የሚከናወነው።
እነዚህ ደግሞ አዳዲስ ደም ለጋሶች የሚገኙበትም ነው።
እነሄኖክ የድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው 'ጂጂ'ን የልደት ቀን በማስመልከት የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል።
"የድምጻዊቷ አድናቂ የሆኑ ከ150 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ደም ለጋሶች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ደም ለግሰዋል" ብሏል።
'የለገስከው ደም ለማን እንደደረሰ ታውቃለህ?' ተብሎ ሲጠየቅ ሄኖክ ምላሹ አጭር ነው 'አላውቅም' የሚል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ሲቀሰቅሱ የገጠመውን ግን አይረሳወም።
'አስር ጊዜ ደም ደም የምትሉት ምን ሆናችሁ ነው?' ያለው ግለሰብ ነበር።
ሚስቱ ትወልድና አዲሷ ልጁ አስቸኳይ ደም ያስፈልጋታል።
ሄኖክ ጋር ደውሎ ይነግረዋል። ሄኖክ በጎ ፈቃደኞችን አስተባብሮ የሚያስፈልገው ደም እንዲሰጥ ያስደርጋል።
የግለሰቡ ልጅም ዳነች።
"በጣም ነው ማመን ያቃተው። ደውሎ ደም መለገስ እንደሚጀምር ነገረኝ። ባለፈው ወር መጥቶ ደም ለግሷል" ይላል ሄኖክ።
ነሐሴ 01/2008 በባሕር ዳር ነዋሪ ላይ ጠባሳውን ቢያሳርፍም እንደነሄኖክ ያሉትን ደግሞ ለሰብዓዊነት አነሳስቷል።















