አፕል በቻይና በ'አፕ ስቶር' ያለውን የቁርዓን መተግበሪያ አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፕል በቻይና ከባለሥልጣናት የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ በዓለም ታዋቂ የሆነውን የቁርዓን መተግበሪያ አነሳ።
'ቁርዓን ማጂድ' የተባለው መተግበሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፕ ሰቶር [የመተግበሪያዎች መገኛ] ላይ የሚገኝ ሲሆን 150 ሺህ የሚጠጉ አስተያቶች ያሉት ነው።
ቢቢሲ መተግበሪያው የተነሳው ሕገ ወጥ የሆኑ ሐይማኖታዊ ጽሁፎችን በማዘጋጀት እንደሆነ ለመረዳት ችሏል።
የቻይና መንግሥት በዚህ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
መተግበሪያው መጀመሪያ ላይ እንዲነሳ መደረጉ የታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ አፕል 'አፕ ስቶር' ላይ ያሉትን መተግበሪያዎች በሚቆጣጠረው ድረ ገጽ -አፕል ሴንሰርሽፕ ነበር።
መተግበሪያውን የሠራው ፒዲኤምኤስ ባወጣው መግለጫም "እንደ አፕል ድርጅት ከሆነ 'ቁርዓን ማጂድ' መተግበሪያ ከቻይና ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን የሚጠይቁ ይዘቶችን በማካተቱ ምክንያት በቻይና ካለው አፕ ስቶር ተነስቷል" ሲል ገልጿል።
ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታትም ከቻይና የሳይበር ስፔስ አስተዳዳር እና ከሚመለከታቸው የቻይና ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር እየሞከርኩ ነው ብሏል።
ድርጅቱ እንዳለው መተግበሪያው መነሳቱ በቻይና አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን እንዳይገለገሉበት አድርጓል።
የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ በአገሪቷ እስልምናን እንደ ሐይማኖት በይፋ የተቀበለ ቢሆንም፤ ቻይና በዢንጂያንግ የሚገኙ የዊጋ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብሎም የዘር ማጥፋት በመፈፀም ይከሰሳል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቻይና ዢንጂያንግ የዊጋ የሐይማኖት መሪዎች (ኢማሞች) ኢላማ እንደተደረጉ ቢቢሲ ዘግቧል።
አፕል ስለ መተግበሪያው መውረድ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ነገር ግን ቢቢሲ "በአገሪቷ ሕጎች እንገዛለን፤ አንዳንድ ገዜ ግን ከመንግሥት ጋር የማንስማማባቸው ውስብስብ ጉዳዮች ይኖራሉ" የሚለውን የሰብዓዊ መብቶች ፖሊሲውን እንዲመለከት መርቷል።
ይሁን እንጂ መተግበሪያው በቻይና የትኛውን ሕግ እንደጣሰ ግልጽ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, ከቁርዓን ማጂድ ማስታወቂያ ላይ የተወሰደ
ቁርዓን ማጂድ መተግበሪያ እንደሚለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ35 ሚሊየን በላይ ሙስሊሞች ዘንድ ተዓማኒነት አለው።
ባለፈው ወር አፕል እና ጉግል በእስር ላይ በነበረው የሩሲያ ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫሊይ የተዘጋጀውን የድምፅ መስጫ መተግበሪያ አስወግደዋል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ሁለቱ ድርጅቶች መተግበሪያውን አላወርድም ካሉ ቅጣት እንደሚጥልባቸው አስፈራርተዋቸው ነበር።
ቻይና ትልቅ የአፕል ገበያ ካላቸው አገራት አንዷ ስትሆን የድርጅቱ የአቅርቦት ሰንሰለትም በቻይና ምርት ላይ ጥገኛ ነው።
የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ በአሜሪካ ያሉ ፖለቲከኞች ስለአሜሪካ ፖለቲካ ለማውራት አምባገነን ናቸው፤ ስለቻይና ሲወራ ደግሞ ዝምታ ይመርጣሉ ሲሉ ከሰዋል።
ሥራ አስፈጻሚው "የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2017 ሰባት ሙስሊም አገራትን አግደዋል፤ ነገር ግን በተቃራኒው በቅድመ ምርመራ እና በሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ ያለውን አያያዝ በተመለከተ የቻይና መንግሥትን ከሰዋል" ሲሉ ለንግግራቸው ምሳሌ አጣቅሰዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አፕል ቲያናንሜን ሰኩየር፣ የቻይና መንፈሳዊ ንቅናቄ ፋሉን ጎንግ፣ ዳላይ ሌማ፣ የቲቤት እና የታይዋን ነጻ መውጣትን በተመለከተ ውይይት የሚካሄድባቸውን መተግበሪያዎች ማንሳቱን ኒዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
በ'አፕል ሴንሰርሽፕ' የፕሮጀክት ዳሬክተር የሆኑት ቤንጃሚን እስማኢል "አሁን ላይ አፕል ወደ ቤጂይንግ የቅድመ ምርመራ መሥሪያ ቤትነት ተቀይሯል" ሲሉም ከቻይና መንግሥት እየደረሰባቸው ያለውን ጫና ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንትም አፕል በቻይና ታዋቂ የሆነውን 'ኦሊቭ ትሪ ባይብል' የተሰኘ ሐይማኖታዊ መተግበሪያን አውርዷል። ድርጅቱ ከቻይና መንግሥት እንዲያሟላ የተጠየቀው ነገር በመኖሩ መተግበሪያውን ራሱ እንዳወረደው ለቢቢሲ ገልጿል።
ባለፈው ወር በቻይና 'ፈቃድ ባለማሟላት' ባለቤትነታቸው የአማዞን የሆኑ በድምጽ የሚሰሙ መጽሐፎችን (ኦዲዮ ቡክ) እና የፖድካስት አገልግሎት ከአፕ ስቶር ላይ ማውረዱን ማክ ኦብዘርቨር የተሰኘው የዜና ድረ ገጽ አርብ ዕለት አስነብቧል።
ማይክሮሶፍት በበኩሉ በቻይና በሕግ መገዛት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን በመግለፅ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን፣ ሊንክድንን እንደዘጋ ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።
ድርጅቱ እንዳለው ውሳኔው የተላለፈው የአንዳንድ ጋዜጠኞች አካውንት እንዲዘጋ ጥያቄ መቅረቡን ተከትሎ ነው።












