አፕል የደንበኞቹን ፎቶ አይቶ ሕፃናት በዝባዦችን ሊለይ ነው

iPhone

የፎቶው ባለመብት, PA Media

አፕል ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ የሚያደርሱ ደንበኞቹን በአይፎን ስልካቸው አማካይነት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ።

ደንበኞች ፎቷቸውን አይክላውድ ወደተሰኘው ቤተ መዘክር ከመላካቸው በፊት ቴክኖሎጂው ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ ተፈፅሞ ከሆነ ያጣራል።

አፕል እንዳለው ቴክኖሎጂው ይህን መሰል ምስል ካገኘ በሰዎች እንዲጣራ ይደረግና በኋላ ጉዳዩን ለፖሊስ አሳልፈው ይሰጣሉ።

ነገር ግን ይህ የአፕል አዲሱ ቴክኖሎጂ ነፃነትን ይጋፋል የሚል ቅሬታ እየቀረበበት ነው።

ስጋት የገባቸው ሰዎች ቴክኖሎጂው ያልተፈቀዱ ፋይሎችንና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስልካቸው ለያዙ ሰዎች አደጋ ነው ይላሉ።

ባለሙያዎች ደግሞ አዲሱ የአፕል ቴክኖሎጂን መንግሥታት ሕዝባቸው ላይ ለመሰለል ሊጠቀሙበት ይችላሉ ባይ ናቸው።

ቴክኖሎጂው የሚሠራው ከዚህ በፊት ያሉ የሕፃናት ወሲባዊ ብዝበዛ ፎቶዎችን በመጠቀም ነው።

ካስም የተባለው ቴክኖሎጂ ከጠፉና ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች ማዕከል ከሚያገኛቸው ምስሎች እና ከሌሎች ድርጅቶች ያገኛቸውን ፎቶዎችን ይጠቀማል።

ቴክኖሎጂው እኚህን ፎቶዎች በሚገባው መልኩ ወደ ኮድ ይቀይርና በአፕል ምርቶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል።

ግዙፉ ኩባንያ ቴክኖሎጂው የመለየት ኃይሉ መቶ በመቶ ነው ይላል።

ምናልባት ከአንድ ትሪሊዬን ፍለጋዎች አንዱን ቢስት ነው እንጂ ሌሎቹን መንጥሮ የመለየት አቅም አለው ሲል ኩባንያው ይፋ አድርጓል።

ነገር ግን ቴክኖሎጂው ከለየ በኋላ የሰው ልጅ ድጋሚ ፎቶዎቹን እንደሚያጣራና ከዚያ በኋላ ለሕግ አካል ሪፖርት እንደሚደረግ አፕል አስታውቋል።

አፕል ይህን ይበል እንጂ በቴክኖሎጂ ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አልተዋጠላቸውም።

"አፕል የረዥም ጊዜ ዕቅዱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ጠቆም አድርጎልናል። ቴክኖሎጂው ከታሰበው ውጭ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል" ይላሉ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲው ማቲው ግሪን።

አፕል አዲሱን ቴክኖሎጂ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ይፋ ለማድረግ አቅዷል።