ግብፅ ያልተከተቡ መምህራን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይገቡ ከለከለች

አንዲት ተማሪ በክፍል ውስጥ ከእጅ ንጽህና መጠበቂያ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በግብፅ በሁለት ሳምንት ውስጥ ትምህርት ይጀመራል

የግብፅ የትምህርት ሚኒስቴር ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው ወይም መከላከያ ክትባት መውሰዳቸው ያልተረጋገጡ መምህራንና ሠራተኞች ወደ ትምህርት ተቋማት እንዳይገቡ እግድ ጣለ።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ግብፅ የበሽታውን በትምህርት ተቋማት ውስጥ መስፋፋት ለመግታት ስትል ነው ይህንን እርምጃ የወሰደችው።

በዚህም መሠረት በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም የትምህርት ደረጃ ላይ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችና መምህራን መከተብ ወይም በየሳምንቱ ውድ የሆነውን ምርመራ ማድረግ አለባቸው።

ይህም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠራተኞችና መምህራንን የሚያካትት ሲሆን ወደእነዚህ ተቋማት ለሥራ ከመሄዳቸው በፊት ለበሽታው መከላከያ የሚውለውን ክትባት ሙሉ ለሙሉ መከተባቸው አሊያም ደግሞ ተመርምረው ከበሽታው ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ታሪቅ ሻውቂ እንደተናገሩት የኮቪድ መከላከያ ክትባት ያልወሰዱ የትምህርት ተቋማት ሠራተኞች በየሳምንቱ 100 ዶላር ያህል በመክፈል ምርመራ አድርገው ውጤታቸውን ማሳወቅ አለባቸው።

ከአገሪቱ መንግሥት የወጣ ይፋዊ አሃዝ እንደሚያመለክተው በግብፅ ውስጥ ከሚገኙ መምህራን መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት የወረርሽኑ መከላከያ ክትባትን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

በግብፅ የትምህርት መረሃ ግብር መሠረት አዲሱ የትምህርት ዓመት በሁለት ሳምንት ውስጥ ይጀመራል።

ግብፅ ከአፍሪካ አገራት መካከል በኮሮናቫይረስ ምክንያት በርካታ ሰዎች ከሞቱባቸው አገራት ውስጥ የምትመደብ ሲሆን አስካሁን ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሰበብ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በሕዝብ ብዛትም በአህጉሪቱ ከናይጄሪያና ከኢትዮጵያ በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን አስካሁን ከ5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧን የወረርሽኙን መከላከያ ሙሉ በሙሉ ከትባለች።